የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 ሀዲያ ሆሳዕና

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአዲስ አበባ የመጨረሻው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገዋል።


አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

ጨዋታው እጅግ ጠንካራ ጨዋታ ነው። ሀዲያ ሆሳዕና በሁሉም ረገድ ጠንካራ ቡድን ነው። ሆኖም ግን ጨዋታውን ተቆጣጥረን ለመጫወት ጥረት አድርገናል ፤ በ 90 ደቂቃ ውስጥ ያየነው የጨዋታ እንቅስቃሴም ያሳየን ያንን ነው። ሆኖም ኃይል የቀላቀለ ጨዋታ ይጫወቱ ስለነበር ዳኛው በአግባቡ ጠብቆናል ብዬ አላስብም። ሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ 20 ፣ 25 ደቂቃዎች ላይ ነበር ወደ ፊት ጫና ያደረግነው። ያው ጎል አስተናግደናል ፍፁም በማያሳምን ሁኔታ። ያገኘነውን አጋጥሚ ወደ ጎል መቀየር ይገባን ስለነበርም ነው የአጥቂ ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ለማስገባት የሞከርነው። ያም ተሳክቶልን ጎል ማግኘት ችለናል።

ጎሉ ላይ ስላላቸው ቅሬታ

ግልፅ ነው በየጨዋታዎቹ የሚታዩ ነገሮች አሉ። እኔ ዳኞችን መመዘን አልችልም። የዳኞች ኮሚቴ አለ ይመስለኛል ጨዋታውን የሚገመግም። ይሄንን ለእነሱ ነው የምተወው። ነገር ግን ማንም ተመልካች እንደሚመለከተው ጎል ያስተናገድንበት መንገድ ፍትሀዊ ነው ብዬ አላስብም።

ከጨዋታ ውጪ ነው እያሉ ነው ?

በትክክል !

አሰልጣን አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው

ደህና ነው ለክፉ አይሰጥም። በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ነፃ ጨዋታ ነው የነበረው። እኛም ማሸነፉን ስለፈለግን ከፍተን ነበር የተጫወትነው ፤ ያሰብነው አልተሳካም። ጎረቤታሞችም ነን ፤ ዓመት በዓልም ስለሆነ ሳንቀያየም ነው ውድድሩ ያለቀው።

ከተከታታይ ድል በኃላ ነጥብ ስለመጋራት

ወደ ውድድሩ ስንገባ አንዳችም የወዳጅነት ጨዋታ አላደረግንም። ይህንን እንደወዳጅነት ጨዋታ ነው የምናየው። ምን ጥሩ ነገር ነበር ? ምን ደካማ ጎን ነበር ? ብለን አሁን ቡድኑ እያሳየ ያለው ነገር ጥሩ ስለሆነ ለተሻለ ውድድር ነው የምንሄደው። ትልቁ ፍልሚያ የሚጠብቀን በሚቀጥለው ነው ፤ አጨራረሱን ማሳመር ያስፈልጋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ