ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ አቃቂን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አምስተኛ ሳምንት የበዐል ዕለት ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተቀይራ በገባችው ምንትዋብ ዮሐንስ ጎል አቃቂ ቃሊቲን 1 ለ 0 ረቷል፡፡

10፡00 ሲል በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሳር ላይ በጀመረው የገና በዐል የአምስተኛ ሳምንት የቀኑ ሁለተኛ ጨዋታ ብዙ የግብ አጋጣሚዎች ያልተፈጠሩበት እና የጠሩ የግብ ዕድሎች ሳስተው የታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ ገፅታ ነበር፡፡መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ታጥሮ የታየው የአቃቂ የአጨዋወት መንገድ ሁነኛ አጥቂን በሜዳ ላይ ይዞ ባለመገኘቱ ጥቂት የፈጠሯቸው ዕድሎች ሊጠቀሙባቸው አልቻሉም። ቤዛዊት ንጉሴ አስረኛ ደቂቃ ላይ ሞክራ የኤሌክትሪኳ ግብ ጠባቂ ትዕግስት አበራ ያደነችባት ብቸኛው የክለቡ ሊጠቀስ የሚችል ዕድል ነበር፡፡

ወደ ቀኝ በኩል ወደ ልድት ቶሎአ በሚጣሉ ነገር ግን ፍፁም ደካማ በነበረው የማጥቂያ መንገዳቸው ወደ አቃቂ የግብ ክልል ለመድረስ የታተሩት ኤሌክትሪኮች በተመሳሳይ እንደ አቃቂ ደካማ የፊት መስመርን ይዘው የነበረ በመሆኑ ከግብ ጋር ተራርቀው ታይተዋል ይሁን እንጂ ልደት ቶሎአ 44ኛው ደቂቃ ለማሻማት አስባ አቅጣጫዋን ቀይራ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችዋ ኳስ የክለቡ ብቸኛ ዕድል ነበረች፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ የጨዋታው እንቅስቃሴ ተዳክሞ በታየበት አርባ አምስት አሰልጣኝ መሠረት ማኔ አከታትላ ቀይራ ያስገባቻቸው ተጫዋቾች ቡድኑን በተወሰነ መልኩ ያነቃቃው ቢሆንም የጎላ ሊባል የሚችል ጫናን ግን ማሳደር አልቻሉም በተለይ እጸገነት ብዙነህን ከቀኝ መስመር ተከላካይነት ወደ መሀል ሜዳው ካመጡ በኃላ የነበራቸውን ክፍተት በተወሰነ መልኩ ሊቀርፉ ችለዋል፡፡ በአንፃሩ አቃቂ ቃሊቲዎች በእንቅስቃሴ የማይታሙ የነበረ ቢሆንም በነበረባቸው ፍፁም ደካማ የሳጥን ውስጥ ውሳኔ በተቃራኒው ጎል እንዲያስተናግዱ ረድቷቸዋል፡፡

73ኛው ደቂቃ ላይ ልደት ቶሎአ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ስታሻግር የአቃቂ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ባሳዩት ደካማ ቦታ አያያዝ ተቀይራ የገባችሁ ምንትዋብ ዮሐንስ በጥሩ አጨራረስ ኳሱን ተጠቅማበት በቀሪው ደቂቃ ምንም የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1 ለ 0 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የኤሌክትሪኳን ተከላካይ እታፈራሁ አድርሴን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ