ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

የስድስተኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋች ነክ ጉዳዮችን እነሆ !

👉ቃሉን አክባሪው አቡበከር ናስር

ኢትዮጵና ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጉት ተጠባቂው ጨዋታ አስቀድሞ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ የነበረው አቡበከር ናስር በጨዋታው “ከአንተ ጎል እንጠብቅ ወይ?” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ይህን ብሎ ነበር

“አዎ ግድ ነው። ምክንያቱም በኮከብ ጎል አግቢነቱ ፉክክር ውስጥ አለሁ። ደግሞም ለማሸነፍ ነው የምንገባው። በዚህ ጨዋታ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጌ በሸገር ደርቢ የመጀመርያ ጎሌን አስቆጥሬ እወጣለሁ ብዬ ተስፋ አድርጋለው።” ሲል ሀሳቡን ሰጥቶ ነበር። ታድያ የመጀመርያ ግቡን ለማስቆጠር አልሞ ወደ ሜዳ የገባው አቡበከር ቃሉን ጠብቆ በደርቢው ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ከማስቆጠር አልፎ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።

በፊት አጥቂነት ሲጀምር የተሻለ ውጤታማ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው አቡበከር ፍጥነቱ፣ ድፍረቱ፣ ተጫዋቾች ላይ ኳስ ይነዳበት የነበረው መንገድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ፈተና ሆኖ በዋለበት ጨዋታ በትንሽ ዕድሜው የትልቁን ኢትዮጵያ ቡና ፊት መስመር ብሎም ቡድኑን በአምበልነት መምራቱ ከዕድሜው በላይ የበሰለና በትውልዶች መካከል የተገኘ እንቁ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል።

👉የማታሲ ቀይ ካርድ እና የምትኩ ለዓለም ብርሃኑ ስህተት

ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን 3-2 በረቱበት ጨዋታ ለ80 ያክል ደቂቃዎች በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ቢጫወቱም በከፍተኛ ጥረት በሁለት አጋጣሚዎች ከመመራት ተነስተው አቻ በመሆን ከደርቢው ጨዋታ አንድ ነጥብ ለመውሰድ ተቃርበው የነበሩት ፈረሰኞቹ በመጨረሻው ደቂቃ ለዓለም ብርሃኑ በሰራው ስህተት የቡድኑ ልፋት መና ቀርቷል።

በ2012 ወር ጥቅምት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ጉዳት ካስተናገደ ወዲህ ከሜዳ ርቆ የሰነበተው ለዓለም ብርሃኑ ከ14 ወራት ገደማ በኃላ ወደ ሜዳ በይፋዊ የነጥብ ጨዋታ በተመለሰበት የማክሰኞው ጨዋታ እንዳለመታደል ሆኖ ቡድኑን ዋጋ በማስከፈል መጀመሩ ተጫዋቹን ዕድለ ቢስ ያደርገዋል።

በተያያዘም ፓትሪክ ማታሲ በሸገር ደርቢ ቀይ ካርድ ሲመለከት ይህ ለሁለተኛ ጊዜው ሲሆን በ2011 የስምንተኛ ሳምንት ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙበት እና 0-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ እንደ ዘንድሮው ሁሉ አቡበከር ናስር ላይ በፈፀመው ጥፋት በተመሳሳይ የዕለቱን ጨዋታ በመሩት የኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ቀይ ካርድ ሰለባ መሆኑ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል።

👉 ወደ ደጋፊነት የተቀየሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች

አቡበከር ናስር በሸገር ደርቢ በ90ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ ካስቆጠረ በኋላ በተቀሩት ደቂቃዎች በቀኝ ጥላ ፎቅ በኩል ተቀምጠው የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጠባባቂ ተጫዋቾች ጨዋታውን ከታደሙት የክለባቸው ደጋፊዎች ጋር በመሆን ደስታቸውን በጋራ የገለፁበት መንገድ የሳምንቱ አስገራሚ ክስተት ነበር።

ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበሩት ጥቂት ደቂቃዎች ተጫዋቾች ከደጋፊቻቸው ጋር በመሆን የክለባቸውን የተለያዩ ዝማሬዎች በአንድነት ያዜሙበት የነበረው መንገድ እና በቡድን አባላቱ ላይ ይታይ የነበረው የደስታ ስሜት ውጤቱ ለቡድኑ ምን ማለት እንደነበረ በግልፅ የሚያሳይ አጋጣሚ ነበር።

👉 ከደጋፊዎች የሚሰነዘር ተቃውሞና የተጫዋቾች ግብረመልስ

በ6ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን ከሰበታ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከውጤቱ ይልቅ ትኩረት የሚስቡ የሜዳ ውጪ ጉዳዮችን ያስመለከተን ጨዋታ ነበር።

ቡድናቸው አስቀድሞ ግብ በማስተናገዱ የተከፉት በስታዲየም የታደሙ የሰበታ ደጋፊዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ከክለባቸው አመራሮች እስከ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች የደረሰ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተስተውሏል። ታድያ በዚህ ተቃውሞ ደስተኛ ያልነበሩት እና በጨዋታው ተቀይረው ከሜዳ ወጥተው በተጠባባቂዎች ወንበር ላይ የነበሩት እስራኤል እሸቱ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ከደጋፊዎች ጋር ከረር ያለ የቃላት ልውውጦችን ሲያደርጉ ተስተውሏል።

በተመሳሳይ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የአቻነቷ ግብ በተቆጠረበት መንገድ ደስተኛ ያልነበሩ የተወሰኑ የጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎች የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ መጓጓዣ አውቶብሳቸው በሚገቡበት ወቅት ተቃውሞው ያነጣጠረበት ግብ ጠባቂው ጄኮ ፔንዜ ከደጋፊዎች ጋር ለፀብ የተጋበዘበት መንገድ ሌላኛው ክስተት ነበር።

እርግጥ ነው የተቃውሞዎቹ አግባብነትን ወደ ጎን ትተን ሁኔታውን ስንመለከት ተጫዋቾች መሰል አጋጣሚዎች በሚፈጠሩበት ወቅት ስሜታቸውን ተቆጣጥረው ሁኔታዎቹን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ በስክነት እና በብልጠት ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም ተጫዋቾች ስሜታቸውን እንዲገዙ በማድረግ ረገድ ክለቦች ተጫዋቾቻቸው ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

👉እንደገና የተወለደው ጀማል ጣሰው

በ2005 በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው መሪነት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ አባል የነበረው ጀማል ጣሰው በ2009 በጅማ አባቡና መለያ በቋሚነት ሲጫወት ከተመለከትነው ወዲህ በድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ሜዳ ላይ ከተሰለፈባቸው ደቂቃዎች የሚልቁትን ጊዜያት በተጠባባቂነት ለማሳለፍ ተገዷል።

ዘንድሮ ወደ ወልቂጤ ከተማ ካደረገው ዝውውር በኃላ ግን በቋሚነት በቋሚዎቹ መካከል እየተመለከትነው እንገኛለን። ደፋር እና ለውሳኔዎች ፈጣን የሆነው ግብ ጠባቂው ይህ አጨዋወት ብዙ ጊዜ ራሱንም ሆነ ቡድኑን ለአደጋ ቢያጋልጥም ስኬታማ ከሆነለት ግን ለቡድኑ ከፍተኛ ዋጋ ሲያስገኝለት ይታያል።

በቋሚነት ለመጫወት ከዓመታት በኃላ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመ የሚገኘው ጀማል ጣሰው ዘንድሮ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በተዘነጋበት ሊግ አሁንም ጥሩ ግብ ጠባቂ መሆኑን ዳግም እያስታወሰን ይገኛል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ከሊጉ መሪ ሀዲያ ሆሳዕና አቻ በተለያየበት ጨዋታ ባዳናቸው ኳሶች ቡድኑን በጨዋታው እንዲቆይ ብሎም ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያስቻለበት ብሎም ቡድኑን የመራበት መንገድ የግብ ጠባቂውን ብቃት በግልፅ ያሳየ ነበር።

👉እንደ ወይን እያደር የጣፈጠው ዳንኤል ደርቤ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ባለፉት 10 እና ከዛ አለፍ ላሉ ዓመታት አቋማቸው ሳይዋዥቅ በወጥነት ቡድኖቻቸውን በማገልገል ላይ ከሚገኙ የመስመር ተከላካዮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚቀመጡት ተርታ ይመደባል።

እጅግ የላቀ ፕሮፌሽናል እንደሆነ የሚነገርለት ዳንኤል ደርቤ አሁንም በሀዋሳ ከተማ ቤት ተፅዕኖው የጎላ ነው። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን 4-1 በረቱበት ጨዋታም ዳንኤል ጥሩ የሚባል ቀንን አሳልፏል። አንጋፋው የመስመር ተከላካይ አንድ ጎልን ከርቀት ሲያስቆጥር በተጨማሪም አንድ ጎል የሆነን ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ለረጅም ዓመታት ራሱን ጠብቆ በመጫወት ላይ የሚገኘው የመስመር ተከላካዩ ብዙ መሮጥ እና መታተር በሚፈልገው የመጫወቻ ስፍራው አሁንም ሳይቸገር እየተጫወተ ይገኛል።

👉ዕድለኛ ያልነበረው ፍፁም ዓለሙ

ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 በረታበት ጨዋታ የባህርዳር ከተማ የልብ ምት የሆነው ፍፁም ዓለሙ ዕድለኛ አልነበረም።

በተጋጣሚ ቡድኖች መስመሮች መካከል እየገባ ኳሷችን እየተቀበለ እንዲሁም ተከላካዮች ላይ ኳስን እየነዳ በመሄድ አደጋ በመፍጠር የተካነው ተጫዋቹ በሊጉ በአሁን ወቅት እየተጫወተ የሚገኝ ድንቅ የአጥቂ አማካይ መሆኑን ማስመስከሩን ቀጥሎበታል።

በጨዋታው እንደተለመደው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ፍፁም በሁለት አጋጣሚዎች የግቡ አግዳሚ እንዲሁም በአንድ አጋጣሚ ደግሞ የግቡ ቋሚ ወደ ግብ ያደረጋቸውን ሙከራዎች አምክነውበታል።

👉ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶችን ያዳነው ሶሆሆ ሜንሳህ

ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን 4-1 በረታበት ጨዋታ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የተጋፈጠው ቶጓዊው የሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂ ሁለቱን በአስደናቂ ብቃት ማዳን ችሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የአማኑኤል ተሾመን የፍፁም ቅጣት ምት ያስተናገደው ሜንሳ በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ድቻዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ፀጋዬ ብርሃኑ በመጀመሪያው በድጋሚ እንዲመታ በተደረገበትም ወቅት በአስደናቂ ብቃት ሊያድንበት ችሏል።

👉 የናስር ወንድማማቾች በሸገር ደርቢ

ከሌላው ጊዜ የተለየ ጥሩ ድባብ እና ፉክክር በታየበት የሸገር ደርቢ የናስር ወንድማማቾችን ያህል ትኩረት የሳበ የለም። ታላቅየውና ቡድኑን በአምበልነት የመራው አቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ ከመስራቱ ባሻገር የፍፁም ቅጣት ምት በማምከን እና ለማታሲ በቀይ ካርድ መነሻ በመሆን የጨዋታው ዐበይት ጉዳዮችን ሁሉ ጠቅልሎ ሲወስድ ታናሽ ወንድሙ ሬድዋን ናስር በራሱ ጎል ላይ በማስቆጠር ሌላኛውን ርዕስ የፈጠረ ተጫዋች ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ