ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ የዓመቱን ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ረፋድ ላይ ወላይታ ድቻን የገጠመው የሙሉጌታ ምህረቱ ሀዋሳ ከተማ 4-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል አሳክቷል።

ሀዋሳዎች ከጅማ አባ ጅፋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ዳንኤል ደርቤን በዘነበ ከድር፣ ዳዊት ታደሰን በጋብርኤል አህመድ እንዲሁም መስፍን ታፈሰ እና ላውረንስ ላርቴም በዮሐንስ ሴጌቦን እና ኤፍሬም አሻሞ ተክተዋል። አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ በበኩላቸው ከድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ ባደረጉት በርካታ ለውጥ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የወጣው ስንታየሁ መንግሥቱን በያሬድ ዳርዛ፣ ኤልያስ አህመድን በእንድሪስ ሰዒድ፣ አንተነህ ጉግሳን በአዩብ በቀታ፣ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙን በመክብብ ደገፉ፣ ያሬድ ዳዊትን በመሳይ አገኘሁ እንዲሁም መልካሙ ቦጋለን በአምበሉ ደጉ ደበበ ምትክ ወደ ቀዳሚው አሰላለፍ አምጥተዋል።

በተሟሟቀ እንቅስቃሴ የተጀረመው ጨዋታው ግብ ለማስተናገድ የፈጀው አምስት ደቂቃ ብቻ ነበር። ሀዋሳዎች በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በማምራት ብሩክ በየነ ያቀበለውን ኳስ ከጉዳት መልስ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የተመለሰው መስፍን ታፈሰ መሬት ለመሬት አጠንክሮ በመምታት መሪ መሆን ችለዋል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላም የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ሀዋሳዎች ከጎሉ ጋር በሚመሳሰል የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደፊት በመሄድ በ16ኛው ደቂቃ ብሩክ መትቶ ወደ ውጪ በወጣበት እና በ18ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ በወጣበት ኳሶች የጎል እድል ፈጥረዋል። በ27ኛው ደቂቃ ደግሞ ጥሩ ቀን ያሳለፈው ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ጎልነት ተለውጧል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ድቻዎች በኒት መስመር የነበራቸው አስፈሪነት ጠፍቶ የዋለ ሲሆን በ16ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ አሻግሮለት ያሬድ ደርዛ ከሞከረውና ሶሆሆ ምንሳ ካወጣው ኳስ ውጪ የጠራ እድል መፍጠር አልቻሉም። ያም ሆኖ በ31ኛው ደቂቃ ምኞት ደበበ በያሬድ ደረሰዛ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ተሾመ ወደ ጎልነት ቀይሮ ልዩነቱን አጥብቧል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳዎች እንደመጀመርያው ሁሉ በጥሩ መንገድ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን በ52ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሐንስ በጥሩ ሁኔታ የላከለትን ኳስ ብሩክ በየነ አስቆጥሮ ልዩነቱን አስፍቷል። ጨዋታው በፈለጉት መንገድ የሄደላቸው ሀይቆቹ የተበታተነው የድቻን የኋላ ክፍልን መፈተሻቸውን ቀጥለው ከዳንኤል ደርቤ የተሻገረውን ኳስ መስፍን በግሩም አጨራረስ የዕለቱን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በቀሩት ደቂቃዎች እጅግ የቀዘቀዘ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ ልዮነቱን ለማጥበብ ይህ ነው የሚባልን ጥረት ያላሳዩት ድቻዎች በ67ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሃኑ በግራ ከግራ የሳጥኑ ክፍል ሰብሮ በመግባት ካደረገውና ለጥቂት ወደ ውጭ ከወጣበት ኳስ ውጭ ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በ90ኛው ደቂቃ አወዛጋቢ በነበረው ውሳኔ ወላይታ ድቻው ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ፀጋዬ ብርሃኑ ቢመታም ሜንሳህ ሶሆሆ አድኖበታል። ሆኖም በድጋሚ እንዲመታ ተወስኖ እንደገና በማዳን ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 4-1 የበላይነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ