ሪፖርት | የአህመድ ረሺድ ጎል ለባህር ዳር ከተማ ሦስት ነጥብ አስገኝታለች

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ የመጨረሻ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኃላ በአህመድ ረሺድ ብቸኛ ግብ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመ ልሳን ሱራፌል ጌታቸው፣ ምንያምር ጴጥሮስ እና ኩዌኩ አንዶህን በማሳረፍ በምትካቸው ሄኖክ ኢሳይያስ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና ፍሬዘር ካሣን ሲጠቀሙ በአንፃሩ በባህር ዳር በኩል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ባለፈው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣው ወሰኑ ዓሊ ምትክ ግርማ ዲሳሳ ሲካተት በሄኖክ አወቀ ምትክ ሳላምላክ ተገኝ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ተካቶ ጨዋታውን ጀምሯል።

በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ የነበረና በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጣኖቹን ፍፁም ዓለሙን እና ሙህዲን ሙሳ ላይ የተነጠለጠሉት የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ያልነበሩበት አጋማሽ ነበር።

በሙከራ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ባህርዳር ከተማዎች በ23ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ከቀኝ ሳጥን ሰብሮ የገባው ፍፁም አለሙ ወደ ግብ ልኮ የግቡ ቋሚን ለትማ የተመለሰትበት እንዲሁም በ35ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ የመታውን ኳስ ፍሬው ጌታሁን በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ሙከራ የአጋማሹ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በተጨማሪም ፍፁም ዓለሙ በመጀመሪያ አጋማሽ የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ፍፁም አለሙ ከድሬዳዋ ከተማ ሳጥን ጠርዝ ላይ ካገኙት የቅጣት ምት የተገኘውን ኳስ በተመሳሳይ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ በመለሰበት ኳስ ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመርም እንዲሁ ፍፁም አለሙ ከመስመር የደረሰው ኳስ ከድሬዳዋ ሳጥን ውስጥ ሞክሮ የግቡን አግዳሚ ሸረፍ አድርጋ በወጣችበት ኳስ ነበር ጅማሮውን ያደረገው ፤ ታድያ የባህርዳሮች ተደጋጋሚ ጥረት ፍሬ አፍርቶ አህመድ ረሺድ በ53ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ተነስቶ በግል ጥረቱ ተጫዋቾችን አልፍ ቡድኑን መሪ ያደረገች ማራኪ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በተቀሩት የጨዋታው ደቂቃዎች ባህርዳር ከተማዎች ተቀዛቅዘው ሲታዩ በአንፃሩ በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ በቁጥር እጅግ የሚያንሱት ድሬዳዋ ከተማዎች በ73ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ከተሻማ ኳስ ያገኘውን ኳስ እንደመጣ ሄኖክ ኢሳያስ ሞክሮ ሀሪሰን ሄሱ ካዳነበት ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሲያደርጉ አልተመለከትንም።

በመጨረሻም ጨዋታው ተጨማሪ ግቦችን ሳያስተናግድ በባህርዳር ከተማ የ1-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ