ከፍተኛ ሊግ | ደብረ ብርሀን እና ለገጣፎ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁለተኛ ሳምንት ባቱ ላይ በ9:00 ለገጣፎ ለገዳዲን ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። 

በዚህ ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞ ዳኛ ዓለም ነፀበ በተደረገ የህሊና ፀሎት በተጀመረው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተሽለው የታዩት ደብረ ብርሃኖች ከጨዋታው ጅማሮ አንስተው በተደጋጋሚ ወደ ለገጣፎ የግብ ክልል እየደረሱ ጥቃት ሲነዝሩ በተቃራኒው ለገጣፎዎች ኳስን መስርቶ ለመጫወት የሚደርጉት ጥረት በደብረ ብርሃን የፊት ተሳላፊዎች ሲከሽፍ ቆይቷል። በ6ኛው ደቂቃ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ፊት በመግባት ካሣሁን ሶቦቃ በሞከረው ጥሩ ሙከራ ደብረ ብርሃኖች የመጀመሪያ አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል። ከደቂቃዎች በኋላ ሢሳይ አዳሙ የተከላካዩን እና የግብ ጠባቂውን ስህተት ተጠቅሞ የመታው ጥሩ ኳስ ለጥቂት ወጥታበታለች። ይህ አጋጣሚ ቡድኑን መሪ ማድረግ የምትችል መልካም ዕድልም ነበረች።

በለገጣፎዎች በኩል በአንድ አጋጣሚ የደብረ ብርሃን ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ነፃ ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ወርቁ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አስቀድመው እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ደብረ ብርሃኖች ከሁለቱም መስመር ተሻጋሪ ኳሶች እንዲሁም ከቅርብ ርቀት ላይ ሆነው የሚገኙትን የቆሙ ኳሶች ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ደብረብርሃኖች ብልጫ የወሰዱበት እንቅስቃሴ ማስቀጠል አልቻሉም። በተለይ በቆሙ ኳሶች እና ከመስመር በሚሻግሮቸው የጣፎን መረብ ለመጎብኘት የጣሩት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው የገቡት ጣፎዎች ኳስን ይዞ በመጫወት ከቀኝ መስመር በፍጥነት ወደ ሳጥን በመግባት ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ቢያደርጉም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የለገጣፎ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝን የተመለከቱት የለገጣፎው አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ የአምስት የተጫዋች ለውጥ ቢያደርጉም ግልፅ የማግባት አጋጣሚ የፈጠሩት የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ነበር። ዳዊት ቀለመወርቅ ከግራ መስመር ያሻገረውን በሱፍቃድ ነጋሽ በተረጋጋ ሁኔታ መትቶት በግቡ የግራ አግዳሚ ተጠግታ ወጥታበታለች። በድጋሚ ዳዊት ቀለመወርቅ ከዘካሪያስ ከበደ የተሻገረውን ኳስ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ሙሴ ገብረ ኪዳን አድኖበታል።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ አሰልጣኝ ኃይለየሱስ የነበራቸውን ብልጫ አጠናክረው ከመጠቀም ይልቅ ወደኃላ አፈግፍገው የጥንቃቄ አጨዋወትን በመከተል በመልሶ ማጥቃት መጫወት ምርጫቸው ያደረጉ ሲሆን በዚህ አጨዋወት በ81ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ መሐመድ ዓሊ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጭ በመሆኑ ሳይፀድቅ ቀርቷል። ጨዋታውም ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ