ከፍተኛ ሊግ | ወሎ ኮምቦልቻ ድል ቀንቶታል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁለተኛ ሳምንት ባቱ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ ወልዲያን 2-1 አሸንፏል።

የአካል ንክኪ በበዛበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ተጋጣሚዎች ጨዋታውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ የተሳካ የኳስ ቅብብል ያስመለከቱት ወልድያዎች ከተጋጣሚያቸው እጅጉን በተሻለ መልክ የግብ ክልል ላይ እየደረሱ ጥቃት ሲነዝሩ ቆይተዋል። በተቃራኒው ወሎዎች አልፎ አልፎ በረጅሙ ከሚጣሉ ኳሶች በስተቀር ጫና አልፈጠሩም። ሄኖክ ካሳሁን አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው ገመቹ በቀለ ያዳነው እንዲሁም በ1ኛው ደቂቃ ሙከራ አድርጎ የነበረው ፍፁም ደስይበለው 37ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ይዞ ገብቶ ሳይጠቀምበት በቀረው ኳስ ወልዲያዎች ለግብ ተቃርበው ነበር።

ወሎ ኮምበልቻዎች የመስመር አጨዋወት በመምረጥ በሁለት ኳስ ንክኪ ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ብዙም የተሳካ አልነበረም። ያም ቢሆን በአንድ አጋጣሚ የተከላካዩ ሄኖክ አቻምየለው እና የግብ ጠባቂውን ስህተት ተጠቅሞ ፈጣኑ አጥቂ አቢይ ቡልቲ የመታው ኳስ በግቡ አናት ሲወጣበት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እንዳለማሁ ታደሰ ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂው ያደነበት ተጠቃሽ ሙከራዎቻቸው ነበሩ። አስቀድመው እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር ያልቻሉት ወልዲያዎች ከሁለቱም መስመር ተሻጋሪ ኳሶች እንዲሁም ከቅርብ ርቀት የሚገኙትን የቆሙ ኳሶች ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት በኋላ ወደ ራሳቸው እንቅስቃሴ የተመለሱት ወሎ ኮምበልቻዎች በረጃጅም ኳሶች እና ከቆሙ ኳሶች መነሻነት የተጋጣሚያቸውን መረብ ለመጎብኘት የደረጉት ጥረት የማታ ማታ ሰምሮላቸዋል። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳሱን በርጋታ ይዘው የነበሩት ወልዲያዎች ከመስመር በፍጥነት ወደ ሳጥን በመግባት ጥቃት ቢፈፅሙም በአጥቂዎቻቸው ስህተት ስኬታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። ዮሐንስ ኪሮስ ከግራ ይዞ በመግባት የመታውም ኳስ የግቡን የግራ አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ቀፃባ ፍቅር ማርያም አግኝቶ ቢሞክርም በግቡ አግዳሚ ወጥቶበታል።

በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ሲገቡ የነበሩት ወልዲያዎች በሚጠቁበት ወቅት ሁለት ተከላካዮችን ብቻ በማስቀረት ወደፊት የሚጠጉ መሆኑን የተረዱት ወሎዎች ግብ አስቆጥረዋል። በ67ኛው ደቂቃ እንዳለማው ታደሰ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን የላይኛውን አግዳሚ መትቶ ወደ መረብ አምርቷል። ከግቡ በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ በጣም የተጫኑት ወልዲያዎች በሄኖክ አቻምየለህ የግንባር ኳስ አቻ መሆን ቢችሉም ለተጨማሪ ግብ ነቀለው ሲወጡ በድርሶ መልስ የተገኘውን የግብ ዕድል በ90ኛው ደቂቃ አብዱራሂም ሙስጣፋ አስቆጥሮ ጨዋታው በወሎ ኮምበልቻ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ