የስድስተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ የሚጀምርበትን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
ፋሲል ከነማ በመጨረሻ ደቂቃ ነጥብ መጋራት ከቻለበት የባህር ዳሩ ጨዋታ በኋላ ዳግም ድልን ለማግኘት ከሲዳማ ይገናኛል። ግብ በማስቆጠሩ ረገድ እምብዛም ችግር እየታየበት ያልሆነው ቡድኑ የተነሳሽነት ስሜቱ መዋዠቅ ከፉክክሩ ወደ ኃላ እንዲቀር ምክንያት የሚሆኑ ነጥቦችን እንዳያሳጣው ያሰጋል። በቡድን እንቅስቃሴም ሆነ በግል ብቃታቸው ጨዋታ መቀየር የሚችሉ ተጫዋቾችን የያዙት ዐፄዎቹ እየመሩ በነበሩባቸው ጨዋታዎች ዳግም ጭንቀት ውስጥ መግባት እና በጎዶሎ ለሚጫወቱ ተጋጣሚዎች ክፍተቶችን የመስጠታቸው ነገር ከታክቲካዊ ምክንያቶች ይልቅ ከታታሪነት ማነስ የመጡ ይመስላሉ። የነገ ተጋጣሚያቸው ደግሞ በዚህ ረገድ የተጋጋለ ጊዜ ላይ እንደመገኘቱ ተሻሽለው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ሙጂብ ቃሲም ጥሩ መሻሻል ካሳየው የሲዳማ የመከላከል አደረጃጀት ውስጥ የሚኖረው ፍልሚያ እና ከእነሽመክት ጉግሳ እና ሱራፌል ዳኛቸው እግር ከሚነሱ ኳሶች ሊፈጠሩ የሚችሉት ዕድሎች ለዐፄዎቹ ወሳኝ ይሆናሉ።
ሲዳማ ቡና በብዙ መስዕዋትነት በኋላ ካሳካው የመጀመሪያ ድል በኋላ ከባዱን ጨዋታ ያደርጋል። ሲዳማዎች ግብ ካገኙ በኋላ በስኬታማ መከላከል ከወልቂጤ ሙሉ ነጥብ ማግኘታቸውን ያየ ነገም ተመሳሳይ አጋጥሚ ከተፈጠረ የፋሲል አደገኛ አማካዮችን ክፍተት ላለመስጠት መታገላቸው የሚቀር አይመስልም። የብርሀኑ አሻሞ እና የዮሴፍ ዮሀንስ የመሀል የፈቱዲን ጀማል እና የጊት ጋትኮች የኋላ ጥምረት በዚህ ውስጥ የፋሲልን ከባድ የማጥቃት ሂደት የመጋፈጥ ፈተና ይጠብቃቸዋል። በማጥቃቱ ረገድም በድኑ ከተነቃቃው ዳዊት ተፈራ የመጨረሻ ኳሶችን ሲጠብቅ በጉዳት ይበልጥ የተመናመነው የፊት መስመሩም እስካሁን ከጎል ጋር ያልተገናኘው ሀብታሙ ገዛኸኝን ልዩ በቃት ይፈልጋል። ለሲዳማ ዋና ፈተና የሚሆነው ግን የግራ እና ቀኝ ክንፉን የቡድኑን የማጥቃት መስመር ባሉት ተጫዋቾች ጠግኖ ማቅረቡ ላይ ነው። በዚህም አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በመረጧቸው ተሰላፉዎች የተጋጣሚያቸው መስመር ተከላካዮች የማጥቃት እንቅስቃሴ ተከትሎው ክፍተቶችን የማግኘት የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ፋሲል ከነማዎች የቀኝ መስመር ተከላካያቸው እንየው ካሣሁን መጠነኛ ህመም ያለበት በመሆኑ የመሰለፉ ነገር እርግጥ ባይሆንም ሌላኛው የቦታው ተጫዋች ሰዒድ ሀሰን ከጉዳት ማገገሙ ጥሩ ዜና ሆኖላቸዋል። በሲዳማ በኩል ሦስቱ አጥቂዎች ጫላ ተሺታ ፣ ይገዙ ቦጋለ እና አዲሱ አቱላ በጉዳት ፍቅሩ ወዴሳ ደግሞ በግል ጉዳይ ለጨዋታው አይደርሱም።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በሊጉ እስካሁን 6 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና አራት በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። በቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ፋሲል ከነማ አሸንፏል። ሲዳማ 10 ሲያስቆጥር ፋሲል 6 ማስቆጠር ችሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
እንየው ካሣሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ
ሽመክት ጉግሳ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሳሙኤል ዮሐንስ
ሙጂብ ቃሲም
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
መሳይ አያኖ
ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ጊት ጋትኮች – ግሩም አሰፋ
ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ዮሴፍ ዮሐንስ
ተመስገን በጅሮንድ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
© ሶከር ኢትዮጵያ