የከፍተኛ ሊጉ የምድብ ለ ክለብ ሻሸመኔ ከተማ ትላንት ከካፋ ቡና ጋር ለነበረው ጨዋታ የኮቪድ 19 የምርመራ ውጤትን ይዞ ባለመቅረቡ በፎርፌ ተሸናፊ ሆኗል፡፡
በሀዋሳ እየተደረገ ባለው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ትላንት ጠዋት 2:00 ላይ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ሻሸመኔ ከተማን ከካፋ ቡና የሚያገናኝ መርሀ ግብር ነበር፡፡ሆኖም በጨዋታው ዕለት ሁለቱም ቡድኖች ሜዳ ላይ መገኘት የቻሉ ሲሆን የካፋ ቡና ክለብ ተጫዋቾቹን ኮቪድ 19 ያስመረመረበትን ውጤት ይዞ የቀረበ ሲሆን የሻሸመኔ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ግን ይህን ሳያደርግ ለጨዋታው መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዕለቱ የነበሩ አወዳዳሪ አካላት የጤና ህጉን ጠብቆ ተሟልቶ የቀረበውን ካፋ ቡናን ሜዳ ላይ ለተጫዋቾቹ ፍተሻን ካደረገ እና ወደ ሜዳ ከገቡ በኃላ በዕለቱ ሰላሳ ደቂቃ ሳይጠበቅ በጤና ፕሮቶኮል መመሪያ መሠረት ክለቡን ማሰናበቱን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ እና የጤና ኮሚቴው በተቀመጠው መመሪያ መሠረት የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን አልጠበቃችሁም በማለት የዳኞችን እና የዕለቱን ኮሚሽነር ሪፖርት ከተመለከተ በኃላ ሻሸመኔ ከተማ በፎርፌ ተሸናፊ ካፋ ቡና በበኩሉ የጨዋታው አሸናፊ ሆኖ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል እንዲመዘገብለት ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ