ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል

በቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየርሊግ ስድስተኛ ሳምንት የረፋድ ጨዋታ ፋሲል ወደ አሸናፊነት የተመለሰበተሰን የ2-0 ድል ሲዳማ ቡና ላይ አሳክቷል።

በፋሲል ከነማ በኩል ከባህር ዳር ጋር አቻ ከተለያየው የመጀመርያ አስራአንድ በእንየው ካሣሁን እና በረከት ደስታ ምትክ ሰዒድ ሀሰን እና ሀብታሙ ተከስተን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ሲመልሱ በሲዳማ ቡና በኩል ጊት ጋት፣ ተመስገን በጅሮንድ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ እና አዲሱ አቱላ ወጥተው ላውረንስ ኤድዋርድ፣ አማኑኤል እንዳለ፣ ያስር ሙገርዋ እና እሱባለው ሙሉጌታ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

የተቀዛቀዘ አንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል በታየበት በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ሲዳማዎች በጥልቀት በመከላከል የፋሲልን የማጥቃት ተጫዋቾች መቆጣጠር ሲችሉ የኳስ ቁጥጥሩን በተሻለ ይዘው ሲጫወቱ የነበሩት ፋሲሎች ከክፍት ጨዋታ የጎል ዕድል ለመፍጠር የተቸግረው ውለዋል። በዚህም በ7ኛው ደቂቃ አምሳሉ ከቀኝ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ አግዳሚውን ጨርፎ ሲወጣበት በ18ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ያሻማውን ቅጣት ምት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሳመኤል በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በዛሬው ጨዋታ ከጉዳት መልስ ወደ አሰላለፉ የተመለሰው ሰዒድ ሀሰን አማኑኤል እንዳለ በሰራበት ጥፋት ትከሻው ላይ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን ተቀይሮ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል አምርቷል።

ከመከላከል ባሻገር እጅግ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያሳዩት ሲዳማዎች ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን የጥንቃቄ አጨዋወታቸውም ጎል ከማስተናግ አላተረፋቸውም። በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከተጋጣሚ ነጥቆ ወደ ሲዳማ የጎል ክልል የላከው ኳስ የመሳይ አያኖ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ሙጂብ ጋር ደርሶ አጥቂው የዓመቱን ሰባተኛ ጎል አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ በፋሲል መሪነት ተጠናቋል።

በተመሳሳይ ደካማ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማዎች የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ቢቀርቡም በእንቅስቃሴያቸው ላይ ለውጥ ያልታየ ሲሆን ፋሲሎች የተሻለ የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። በ64ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ከርቀት መትቶ ወደ ውጪ የወጣበትና የሲዳማ ተከላካዮች ስህተትን ተጠቅሞ ሳሙኤል ዮሐንስ በ66ኛው ደቂቃ በቀኝ እግሩ መትቶ መሳይ ያወጣበት ሙከራም የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም እንደ መጀመርያዎ አጋማሽ ሁሉ ለተጋጣሚያቸው አስቸጋሪ ያልነበሩ ሲሆኑ በተቃራኒው ፋሲሎች በጭማሪ ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ይዘውት የሄዱትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ከቀኝ የሳጥኑ ጠርዞ አካባቢ በመምታት ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በፋሲል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ