ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን 2-0 ከረታበት የቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን ብለዋል።
ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
ስለ ጨዋታው
ውጤቱ በጠበቅነው ደረጃ ነው ማለትም እንቅስቃሴያችን በሚፈልገው ደረጃ ነው ማለት ባልችልም ትልቁ ሀሳባችን የነበረው ወደ አሸናፊነት ለመመለስና ከሻምፒዮኖቹ ተርታ መመደብ አለብን የሚል ነበር። ይህን አሳክተናል። በመጀመርያ አጋማሽ ተጫዋቾቼ ላይ ወደ ጎል ለመጠጋት ችኮላ ነበር። ያ ደግሞ አልጠቀመንም። ከእረፍት በኋላ ተረጋግተን መጫወት ነበር የፈለግነው። ይሆም ሲዳማዎች ውጤቱን ስለሚፈልጉት ያላቸው እድል ነቅለው መውጣት እንደሆነ ስለሚጠበቅ ነው። የኛዎቹ ውጤቱን ማስጠበቅም ይፈልጋሉ፤ አጥቅተው መጫወትም ይፈልጋሉ። በዛ መካከል ያለው እንቅስቃሴ ነው ዝቅ ያለው። ትልቁ ነገር አሸንፈን መውጣታችን ጥሩ ነው። የማሸነፍ መንፈሳችን መመለስ ነው ቀጣይ ጨዋታዎችን ሊያስተካክል የሚችለው።
ስለ ጅማው ውድድር ዝግጅት
የጅማውን እዛው ሄድን ነው የምናየው። ሜዳው፣ አየሩ፣ የምንጫወትበት ሰዓት እነዚህ ሁሉ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። ቀጣይ ተጋጣሚያችን ተከታታይ ጨዋታ ያሸነፈው ሆሳዕና ነው። ትልቅ ፈተና ይጠብቀናል። አሸንፈን ወጀ ጅማ መሄዳችን በስነቦና ረገድ ጥሩ ጥንካሬ ይፈጥርልናል ብዬ አስባለሁ።
ቢሸነፉ ኖሮ ቦታውን ስለማጣት…
የሚባለው ነገር ለኔም እንቆቆልሽ ነው። እስካሁን ማኔጅመንቱ፣ ተጫዋቾቹ እና ቴክኒክ ስታፉ ሁሉም ከጎኔ ነው ያሉት። በእርግጥ ውስን ግለሰቦች የራሳቸው ስሜት ሊኖራቸው ይችላል፤ ትልቁ እና የሚቀድመው ግን ፋሲል ነው። የፋሲል አሰልጣኝ ሆኜ እየሰራሁ ሳለ የምሸኝ ከሆነም በክብር ነው መሸኘት ያለብኝ እንጂ ማንም እንደፈለገ የሚያደርግበት መንገድ የሚኖር አይመስለኝም። ለቡድኑ ካልጠቀምኩ የሥራው አካል እስከሆነ ድረስ መልቀቄ ምንም ችግር የለውም። ነገር ግን አሁንም ለክለቡ ትልቅነት ከአመራሮችም፣ ከተጫዋቾቹም፣ ከስታፉም ጋር በመሆን የምችለውን እየሰራሁ ነው። እንደዛ ሊታሰብ ቢችልም እኔ ግን እንደዛ አስቤው አላውቅም።
ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ስለጨዋታው
እንቅስቃሴያችን ወደፊት ሲሄድ የተገደበ ነበር። ከጨዋታው በፊትም እንደተናገርኩት የፊት መስመር ተጫዋቾች በጉዳት ባመኖራቸው ኳሶች ወደፊት ይሄዳሉ። ለነሱ ተከላካይ ግን አስቸጋሪ አልነበሩም። ያሰብነው ጎላቸችንን ጠብቀን በተገኙ አጋጣሚዎች እድል ለመፍጠር ነበር። ግን በተሳሳትናቸው ኳሶች ሁለት ጎሎች ተቆጥረውብናል። ፊት ላይ ማንንም መውቀስ አይቻልም። ተከላካዮቹን ነው ወደፊት አድርገን ስናጫውት የነበረው። መጨረሻ ላይ እንደውም አማካዩ ዳዊት ተፈራን በመስመር አጥቂነት አጫውተነዋል። የፊት መስመር ተሰላፊዎች አለመኖር እጅግ በጣም ዋጋ አስከፍሎናል።
እነሱ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተሽለው ሳይሆን የኛ የፊት መስመር ጫና ስላለፈጠረባቸው በረጃጅመም ኳሶች ለመውጣት ሲሞክሩ ነበር። ግን ያንን ለመቆጣጠር ከእረፍት በኋላ የበለጠ ኳስ ተቆጣጥረን ጫና ለመፍጠር ነበር ያሰብነው። ሆኖም ጎል ማስቆጠር አልቻልንም። ለማጥቃት በሄድንበት ጊዜ በተከላካዮቻችን የአቋቋም ስህተት በድጋሚ ተቆጥሮብናል። ጨዋታው መጥፎ ባይሆንም በሲዳማ በኩል ለመጀመርያ ጊዜ ጫና ሳንፈጥር የተጫወትንበት ጨዋታ ነበር
በቀጣይ ውጤቱን ስለማስተካከል
ቡድን ስትሰራ እቅድ ይኖርሀል። ግን እንደ እቅዳችን ተጫዋቾቹን በተሟላ ሁኔታ ባለፉት ሦስት አራት ጨዋታ መጠቀም አልቻልንም። እነሱ ከዚህ በኋላ ይደርሳሉ። ያኔ ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ። ሌላው ውጤቱን ለማሻሻል ጠንክሮ መሥራት ነው የሚጠበቅብን።
© ሶከር ኢትዮጵያ