ከፍተኛ ሊግ | መከላከያ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁለተኛ ሳምንት ባቱ ላይ 4:00 ሲቀጥል መከላከያ በሳሙኤል ሳሊሶ ሐት-ትሪክ ታግዞ ፌዴራል ፖሊስን 3-0 አሸንፏል።

ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተሽለው የታዩት መከላከያዎች ምንም እንኳ ለጎል የቀረቡ ጠንካራ ሙከራዎች ባይሆኑም ከጨዋታው ጅማሮ አንስተው በተደጋጋሚ ወደ ፌዴራል ፖሊስ የግብ ክልል እየደረሱ ጥቃት ሲነዝሩ ቆይተዋል። በ1ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ የቀድሞ የ2010 ኮኮብ አግቢ ዘካርያስ ፍቅሬ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂውን አቅም የፈተሸበት ነበር።

ከመጀመርያው ሙከራ በኋላ ተጨማሪ ሙከራዎች ለማየት ረጅም ደቂቃዎች የወሰዱ ቢሆንም የእንቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው መከላከያዎች በ37ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል። ሳሙኤል ሳሊሶ የተከላካይ ስህተት ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ የመታው ኳስ የግቡ መረብ ላይ በማረፍ ጦሩን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ መጠናቂያ ላይ ደግሞ በኃይሉ ግርማ ያሻማውን ኳስ በድጋሚ የተከላካዮች እና በግብ ጠባቂው ስህተት ታክሎበት ሳሙኤል ሳሊሶ አስቆጥሮ በጦሩ 2-0 መሪነት አርፈዋል።

ከእረፍት መልስ ኦሜድላዎች በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የጎቾ ክልል በተደጋጋሚ በመገኘት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ከመስመር በፍጥነት ወደ ሳጥን በመግባት ጥቃት ሲሰነዝሩ የነበሩት መከላከያዎች በዚህም አጋማሽ ተጨማሪ ግብ አግኝተዋል። በ75ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ በቀላሉ ወደ ግብ ክልሉ የላከው መረብ ላይ አሳርፎ ሐት-ትሪክ በመስራት ጨዋታው በጦሩ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

መከላከያ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ማስመዝገብ ሲችል ሳሙኤል ሳሊሶ በአዲሱ የውድድር ዘመን ሐት-ትሪክ የሰራ የመጀመርያ የከፍተኛ ሊግ ተጫዋች መሆን ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ