የአዲስ አበባው የመጨረሻ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል

በስድስተኛው ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር ወልቂጤ እና ሀዲያ ሆሳዕና አንድ አቻ ተለያይተዋል። ሆሳዕናም ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ ጥሏል።

ወልቂጤዎች በሲዳማ ከተሸነፉበት ጨዋታ አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሥዩም ተስፋዬ እና አሚን ነስሩን በተስፋዬ ነጋሽ እና ዳግም ንጉሤ ሲተኩ ፊት መስመር ላይ በአብዱራሀማን ሙባረክ ቦታ ሄኖክ አየለን አሰልፈዋል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ዱላ ሙላቱን በካሉሻ አልሀሰን፣ ሄኖክ አርፊጮን በመድሀኔ ብርሀኔ በመተካት ገብተዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ ሙከራዎች የታዩ ሲሆን ገና በሁለተኛው ደቂቃ ሄኖክ አየለ ከርቀት የተላከለትን ኳስ የግብ ጠባቂ አቋቋም ተመልክቶ በቀጥታ መቶት የጎሉ አግዳሚ ገጭቶበት ወጣ እንጂ ወልቂጤን ቀዳሚ ለማድረግ በእጅጉ ቀርቦ ነበር። ምላሽ ለመስጠት ወደፊት የተጓዙት ሆሳዕናዎችም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ቢስማርክ ከርቀት አክርሮ መትቶ ጀማል ባወጣበት ጠንካራ ኳስ የወልቂጤን ጎል ፈትሸዋል።

ጨዋታው በወልቂጤ የኳስ ቁጥጥር እና በሆሳዕና መልሶ ማጥቃት ቀጥሎ ፍሬው ሰለሞን በ20ኛው ደቂቃ ወደ ቀኝ መስመር ካጋደለ ቦታ የደረጄ ዓለሙን አቋቋም ተመልክቶ የመታውን ቅጣት ሞት ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በተመሳሳይ በሌላኛው ጥግ ዳዋ ሆቴሳ በ35ኛው ደቂቃ የመታውን ቅጣት ምት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ጀማል ጣሰው አድኖበታል።


ጨዋታው ሲጀመር ለጎል እጅግ ቀርበው የነበሩት ወልቀጤዎች የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንኖች ሲቀሩም ወርቃማ እድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ያሬድ ታደሰ በግብ ጠባቂ አናት አሳልፎ ለማስቆጠር ሞክሮ ደረጄ በቀላሉ ተቆጣጥሮበታል።
በመጠኑ የተቀዛቀዘው ሁለተኛው አጋማሽ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በብዛት ባይታይባቸውም ጎሎችን አስመልክቶናል። በ52ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ያሻገረውን ኳስ የወልቂጤ ተከላካዮች የጨዋታ ውጪ ነው በሚል በተዘናጉበት ወቅት ሳሊፍ ፎፋና ተቆጣጥሮ በተረጋጋ አጨራረስ ሆሳዕናን መሪ አድርጓል።

ከጎሉ በኋላም ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ያልተቸገሩት ወልቂጤዎች አደጋ በመፍጠር ረገድ ተዳክመው ታይተዋል። ያም ሆኖ በ72ኛው ደቂቃ ያደረጓቸው ቅያሬዎች ፈጣን አዎንታዊ ለውጥ አምጥቶላቸው ሄኖክ አየለ ባስቆጠረው ጎል አቻ ሆነዋል። ለጎሉ መገኘት ከግራ መስመር በፍጥነት አምልጦ ኳሱን በማሻገር ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን ሚና ከፍተኛ ነበር።

ከአቻነት ጎሉ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ላይ ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት የነበረስ ፍላጎት ተቀዛቅዞ ሲታይ አሜ መሐመድ በወልቂጤ፣ ቴዎድሮስ በቀለ በሆሳዕና በኩል ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ የሚጠቀስ የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

በአቻ ተጀምሮ በአቻ በተጠናቀቀው የአዲስ አበባው ውድድር ሆሳዕና ከአራት ተከታታይ ድል በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ የጣለበት ሆኖ ሲመዘገብ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከሳምንት በኋላ ጅማ ላይ የሚቀጥሉ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ