ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

6ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻው በነበረው የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸውን ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታዩ ፅሁፋችን ለመዳሰስ ሞክረናል። 

👉የቡናማዎቹ ጣፉጭ ድል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ተጠባቂ በነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ ታግዘው የከተማ ተቀናቃኛቸውን 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለደጋፊዎቻቸው ጣፋጭ የገና ስጦታን አበርክተዋል።

ለዓመታት ከተመለከትናቸው የተፋዘዙ የሸገር ደርቢዎች የተለየ በነበረው በዚሁ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ገና በ10ኛው ደቂቃ ነበር ግብ ጠባቂያቸውን ፓትሪክ ማታሲን በቀይ ካርድ ለማጣት የተገደዱት። በጨዋታውም ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ ወደ መሐል ሜዳ ቀርቦ ሲከላከል ከነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ጀርባ ታፈሰ ሰለሞን ለአጥቂዎቻቸው በሚጥላቸው ቁልፍ ኳሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን በጨዋታና በፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግን በሁለቱም አጋጣሚዎች ከመመራት ተነስተው አቻ መሆን ችለው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀይ ካርዱ መነሻነት እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በጀብደኝነት ጫና ፈጥረው ከመጫወት ይልቅ በራሳቸው ሜዳ ተከማችተው ኢትዮጵያ ቡናዎችን መፈናፈኛ በማሳጣት የጨዋታው መጠናቀቅ የሚያበስረው ፊሽካ እየተጠባበቁ በነበረበት ሰዓት አቡበከር ናስር በለዓለም ብርሃኑን ስህተት የተገኘውን አጋጣሚ ወደ ጎልነት ቀይሮ ለዓመታት አሰልቺ ከነበሩት የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በኋላ የተመለከትነው ደማቁ የሸገር ደርቢ በቡናማዎቹ የበላይነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

ይህም ድሎ ኢትዮጵያ ቡና በፕሪምየር ሊጉ በሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከአራት ዓመታት በኃላ ያሸነፈበት ሆኖ ተመዝግቧል።

👉የሀዲያ ሆሳዕና 100% የማሸነፍ ጉዞ መገታት

በሊጉ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎችን በሙሉ በማሸነፍ አስደናቂ ግስጋሴ ላይ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዚህኛው ሳምንት ይህ የማሸነፍ ጉዞ በወልቂጤ ከተማ ፍፃሜውን አግኝቷል።

በመጀመሪያዎቹ አራት ጨዋታዎች ከነበራቸው አቀራረብ በመጠኑም ቢሆን የተሻለ አዎንታዊነትን ጨምረው ጨዋታውን ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በጨዋታው ያለ ፍርሃት በጀብደኝነት ሲጫወቱ ከነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ብርቱ ፈተና ገጥሟቸው ጨዋታቸውን አንድ አቻ በሆነ ውጤት ለመጨረስ ተገደዋል። በሊጉ ብቸኛዎቹ እስካሁን ሽንፈትን ያላስተናገዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሳሊፉ ፎፋና ግብ ጨዋታውን መምራት ቢችሉም ሄኖክ አየለ ያስቆጠራት የአቻነት ግብ የማሸነፍ ጉዟቸውን ገታለች።

በሊጉ እስካሁን ባደረገጓቸው አምስት ጨዋታዎች ወጥ የሆነ እንቅስቃሴን በማድረግ ተመሳሳይ 14 ነጥቦች ካሏቸው ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ያነሰ ጨዋታን አድርገው ከሊጉ ከአናት በመቀመጥ የአዲስ አበባ ቆይታቸውን መደምደም ችለዋል።

👉 በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር አስገራሚ ተጋድሎን ያሳዩት ፈረሰኞቹ

ተጠባቂ በነበረው የሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ገና በ10ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂያቸው ፓትሪክ ማታሲ አቡበከር ናስር ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመወገዱ ምክንያት ቀሪዎቹን 80 ደቂቃዎች በአስር ተጫዋቾች ለመጨረስ ቢገደዱም በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ያሳዩት ትጋት እጅግ የሚደነቅ ነበር።

በቁጥር ማነሳቸው ያላሰጨነቃቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያ ጨዋታውን ሲጀምሩ ይዘውት ከገቡት የጨዋታ አቀራረብ ዝንፍ ሳይሉ የመጀመሪያውን አጋማሽ አጠናቀዋል። በሜዳው የላይኛው ክፍል ቡናዎች ኳስ እንዳይመሰርቱ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለት አጋጣሚዎች ጫና ፈጥረው መጫወታቸው ፍሬ አፍርቶላቸው ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስተው አቻ የሆኑባቸውን ግቦች አግኝተው ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተው ነበር። በሁለተኛው አጋማሽም ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ በተወሰነ መልኩ ጠቅጠቅ በማለት ወደ መከላከሉ የተሸጋገሩ ቢመስልም በመልሶ ማጥቃት በሙሉ ኃይል እያጠቃ የነበረውን ኢትዮጵያ ቡናን ለመቅጣት ጥረት አድርገዋል።

በዚህ ተጠባቂ ጨዋታ ምንም እንኳን በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ለአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቆይተው በመጨረሻ ደቂቃ በተሰራችው ግለሰባዊ ስህተት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ያሳዩት ተጋድሎ በውጤት ረገድ መና ቢቀርም ለቀጣይ ጨዋታዎች ይህን አስደናቂ ተነሳሽነት ማስቀጠል ከተቻለ ቡድኑን በረጅሙ የፕሪምየር ሊግ ጉዞ ውስጥ በእጅጉ ሊያግዘው ይችላል።

👉 ታትሮ ቢከላከልም ውጤት ማስጠበቅ የተሳነው ጅማ አባ ጅፋር

በ6ኛ የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር እንደቀደመው የጨዋታ ሳምንት ሁሉ አስቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን ቢመራም አሁንም ውጤቱን ማስጠበቅ ሳይችል በድጋሚ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ለመለያየት በቅቷል።

ገና ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ጅማዎች በፊት አጥቂነት ጨዋታውን ያስጀመሩት እና ለብቻው ተነጥሎ ይታይ ከነበረው ሳዲቅ ሴቾ ውጭ ያሉትን ቀሪ ተጫዋቾች ወደ ራሳቸው ሜዳ በተሳበ አደራደር ሁለት የመከላከል መስመሮችን ሰርተው በመከላከል ላይ ተጠምደው ተስተውለዋል።

ይባስ ብሎ ሮባ ወርቁ ባስቆጠራት የቅጣት ምት በመጀመሪያው አጋማሽ መምራት የጀመሩት ጅማዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም በውስን አጋጣሚዎች ይሞክሩት የነበረውን መልሶ ማጥቃትንም እርግፍ አርገው ትተው በመከላከል ላይ ብቻ አለፍ ሲልም የሚያገኟቸውን ኳሶች ከመጠቀም ይልቅ ከራሳቸው ሜዳ በማራቅ ተጠምደው ቢቆዩም በ81ኛው ደቂቃ ፍፁም ገ/ማርያም ባስቆጠራት የግንባር ኳስ ጥረታቸው ሁሉ መና ቀርቷል። ቡድኑ በጥብቅ ሲከላከል እንደመዋሉ ፍፁም ከቅጣት ምት ከተሻማ ኳስ ጎሉን ሲያስቆጥር የነበረበት ነፃ አቋቋምም ግርምትን የሚያጭር ነበር።

በሁለቱም ተከታታይ ጨዋታዎች በአሳዛኝ መልኩ በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ያጡት ጅማዎች ከቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ጀምሮ በለመዱት የጅማ ዩኒቨርስቲ የሚካሄደው ውድድር ይህን አሳዛኝ አጨራረስ ያስቀርላቸው እንደው የምንመለከተው ይሆናል።

👉 እያንሰራራ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ

በ6ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ሳይጠበቅ ወላይታ ድቻ ላይ አራት ግቦችን አስቆጥሮ 4-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

አጀማመሩ ላይ ከፍተኛ የስጋት ዳመና አንዣቦበት የነበረው ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። በሊጉ ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች ምንም ዓይነት የተደራጀ የመከላከልም ሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴን ለማሳየት የተቸገረው ሀዋሳ የመጀመሪያ ድሉን ኢትዮጵያ ቡና ላይ ሲያስመዘግብ በከፍተኛ ታታሪነት እንደ ቡድን እንዴት መከላከል እንደሚችል ሲያሳይ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግሮ በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ምንም እንኳን የወላይታ ድቻ በሽግግሮች ወቅት የነበረው ድክመት እንዳለ ቢሆንም የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድን በማጥቃቱ ረገድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን አስመልክቶናል።

ተስፈኞቹ ሁለቱ የቡድኑ አጥቂዎች ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ በጋራ ሦስት ግቦችን ባስቆጠሩበት እና እርስ በርስ ጥሩ መናበብ ባሳዩበት ጨዋታ የመስመር ተመላላሽነት ሚና የነበራቸው ደስታ ዮሐንስ እና ዳንኤል ደርቤ የሀዋሳን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማሳለጥ ረገድ እጅግ ድንቅ ነበሩ።

ከውጤት ማጣት ቀስ በቀስ እየተላቀቀ የመጣው ቡድኑ አሰልጣኙ “እኛን ይገልፀናል” ባሉት “የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ” እንቅስቃሴ ቡድናቸውን ሜዳ ላይ ለማሳየት የበለጠ ነፃነትን በቀጣዮቹ ሳምንታት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉ግራ የተጋባው ወላይታ ድቻ

በአሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ የሚመራው ወላይታ ድቻ ገና ከወዲሁ ስድስተኛ ሳምንት ላይ በደረሰው ሊጉ ከጨዋታ ጨዋታ እጅግ የተፍረከረከ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል።

ከጅማ አባጅፋር እኩል ሦስት ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ተሽሎ ከሊጉ ግርጌ በአንድ ከፍ ብሎ በአስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በቀላሉ ግቦችን የሚያስተናግድ፣ ከምንም ዕድሎችን መፍጠር የሚችሉ አማካዮች ቢይዝም በፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ደካማ ተግባቦት አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ይገኛል።

በአመዛኙ በሊጉ እምብዛም ልምድ በሌላቸው ተጫዋቾች የተገነባው ድቻ በተለይ ፊት መስመር ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችን የሚፈልግ ቡድን ሲሆን በተጨማሪም ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረጉ ሽግግሮች ወቅቱ ቡድኑ ላይ የሚስተዋለው ቀርፋፋነትን በአፋጣኝ ማረም ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ በቀደመ ጊዜው ወላይታ ድቻ ሲባል በብዙሀኑ የእግርኳስ ቤተሰብ አዕምሮ ላይ የሚመጣው በከፍተኛ የፍላጎት ደረጃ እና ታታሪነት መጫወት፣ የጋለ ቡድን መንፈስ እና ኮስታራነትን በጊዜ ካልመለሰ እጅግ ከባዱን የውድድር ዘመን ፈተና የማለፉ ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ይመስላል።

👉 በጥቂት ተጫዋቾች ለማጥቃት የሚሞክሩት ድሬዎች

በሀገራችን እግርኳስ ውስጥ በስፋት ሰርፆ የሚገኘው እና ማጥቃቱ ለተወሰኑ ጥቂት ተጫዋቾች የተተወ እንዲሁም መከላከሉ ደግሞ የተከላካይ አማካዩን ጨምሮ በተከላካዮች ብቻ የሚከወን አድርጎ የመውሰድ ኃላ ቀር ዝንባሌን በተለይ በድሬዳዋ ከተማ ላይ በጉልህ ማስተዋል የሚቻል ሀቅ ነው።

ምንም እንኳን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በባህርዳር ከተማ 1-0 በተረታበት ጨዋታ በመሐል ተከላካይነት ሚና የሚጫወቱ አራት ተጫዋቾችን በአንድነት ስላሰለፈ ጎልቶ ተነሳ እንጂ ቡድኑ በእስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው ጨዋታዎች እንደ ቡድን የማጥቃት እና የመከላከል ሰፊ ችግሮች ይስተዋልበት ነበር ፤ በተለይ በማጥቃቱ።

ለዚህም አንደኛው ምክንያት የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት እንቅስቃሴውን በማገዝ ረገድ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መሆን ነው። በቀኝ የመስመር ተከላካይነት በተወሰኑት ጨዋታዎች ተሰልፎ ድሬዳዋን ካገለገለው ምንያምር ጴጥሮስ ጥረቶች ውጪ ድሬዳዋ በእስካሁኑ የስድስት ሳምንት የሊጉ ጉዞ ውስጥ ለዝርግ የኃላ አራት ተከላካይ የቀረበ የሜዳ ላይ የተከላካዮችን ቦታ አያያዝ እያስመለከተን ይገኛል።

እርግጥ ነው ምንያምር ጴጥሮስ በንፅፅር ድሬዳዋ ከተማ በስብስባቸው ካሏቸው የመስመር ተከላካዮች የተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ ለማድረግ የሚጠይቁትን አዕምሯዊም ሆነ የአካላዊ ብርታትን መላበሱ በምክንያትነት መቅረብ የሚችል ቢሆንም እንደ ቡድን ወደ ጨዋታ ይዘውት የሚገቡት አቀራረብ በአጠቃላይ ቡድኑ በማጥቃት ወቅት ለሚኖረው የቁጥር ማነስ ዓይነተኛ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል። ከሊጉ ድንቅ የአጥቂ አማካዮች አንዱ የሆነው ኤልያስ ማሞ ላይ ኃላፊነት ማብዛት ተጋጣሚ የተጫዋቹን እንቅስቃሴ በመገደብ ቡድኑን በቀላሉ መቆጣጠር የሚያስችለው ነው። በመሆኑም ድሬ ግቦችን እያስቆጠረ ጨዋታዎችነት በቀጣይነት እያሸነፈ ስለመቀጠል የሚያስብ ከሆነ የማጥቃቱ አማራጮቹን ለማስፋት ይህን ችግር በመመርመር መፍትሔ ሊያበጅ ይገባል።

👉ወደ ድል የተመለሱት ፋሲል እና ባህር ዳር

በ5ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብርቱ ፉክክር በታየበት ጨዋታ አቻ የተለያዩት ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ በዚህኛው ሳምንት ሁለቱም ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከተጋጣሚው እጅግ የተሻለ በነበረበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን በአህመድ ረሺድ የግል ጥረት በሁለተኛው አጋማሽ በተገኘች ግብ ማሸነፍ ችሏል። በዚህም በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው የነበሩት የጣና ሞገዶች ወደ ድል አድራጊነት ተመልሰዋል።

በተመሳይይ ፋሲል ከነማም በሁለቱ አጋማሾች የጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ሙጂብ ቃሲም በግል ጥረቱ እና በሲዳማ የኋላ ክፍል ስህተት ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች መጥፎውን ጊዜሽያለፉ የመሰሉት ሲዳማ ቡናዎችን መርታት ችሏል።

👉 ፍፁም የወረደው ሲዳማ ቡና

በሚሊንየሙ የመጀመሪያ ዓመታት ወደ ፕሪምየር ሊግ ከተቀላቀሉ ወዲህ ምንም እንኳን የተጫዋቾች ጉዳት እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች መቅረብ ቢችሉም የዘንድሮው ሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ከተመለከትናቸው የሲዳማ ቡና ቡድኖች ፍፁም የተዳከመው ነው ቢባል አሳማኝ ይመስላል።

ለወትሮው ቢሆን በፈጣን እንቅስቃሴው የሚታወቀው ቡድኑ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ዘንድሮ እንዳልነበረ የሆነ ይመስላል። በአራቱም የቡድኑ ክፍሎች ላይ በእንከን የተሞላው ቡድኑ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ ይህ ነው የሚባል የመጀመሪያ 11 ተመራጭ ተጫዋቾች እንኳን ለማስመልከት አልቻለም። ይባስ ብሎ ያ በፈጣን አጥቂዎቹ ቡድኖችን እያስጨነቀ ግቦችን የሚያስቆጥረው ሲዳማ በዚህኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 2-0 በተረቱበት ጨዋታ የሚጠቀስ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችል ቀርቷል።

በእርግጥ የተጫዋቾች ጉዳት፣ የፓስፖርት ጉዳይ እና የአዲስ ግደይ መውጣት ቡድኑን በትልቁ አጓድሎት ታይቷል። ሆኖም በፋሲሉ ጨዋታ በአጠቃላይ የቡድኑ መዋቅር እና የአጨዋወት መንገድ ለመለየት ግራ የሚያጋባ ሆኖ ታይቷል። ባሉት ተጫዋቾች ስለ አጨዋወቱ ፍንጭ እንኳ የሚሰጥ ነገርም አልተስተዋለም። ለዚህም በመክፈቻው በባህር ዳር ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ አመዛኝ ተጫዋቾቻቸውን አሰልፈው ግራ አጋቢ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው አስረጂ ሀሳብ ነው።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከጨዋታው በኋላ ሲናገሩ እንደተደመጡት ደካማ እንቅስቃሴ ማድረጉን ማመናቸው በቀጣይ ፈጣን የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ስለመሆናቸው አመላካች ይመስላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ