ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የስድስተኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

በስድስተኛው ሳምንት ላይ ያተኮሩ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎችን እንደሚከተለው አጠናቅረናል።

– በዚህ ሳምንት ስድስት የሊጉ ጨዋታዎች 17 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህ ቁጥር ካለፈው በሁለት ያነሰ ሲሆን በአማካይ በጨዋታ 2.8 ጎሎች ተመዝግበውበታል።

– ከሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ውጪ ሌሎቹ ቡድኖቸች ጎል ሲያስቆጥሩ ሀዋሳ ከተማ በአራት ከፍተኛውን ጎል አስቆጥሯል። ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጎል ያላስተናገዱ ክለቦች ናቸው።

– ከ17 ጎሎች መካከል ሁለት (አቡበከር ናስር እና አማኑኤል ተሾመ) በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥሩ ሁለት ከቅጣት ምት (ሮባ ወርቁ በቀጥታ እና ፍፁም ገብረማርያም በጭንቅላት በመግጨት) አስቆጥረዋል። ሌሎቹ 13 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ የተቆጠሩ ናቸው።

– በዚህ ሳምንት ከሳጥን ውጪ ተመትተው አምስት ሎሎች ተቆጥረዋል። ይህም የዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ነው። 12 ጎሎች ደግሞ ሳጥን ውስጥ ተመትተው ተቆጥረዋል።

– 13 ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ጎሎች ላይ ሲሳተፉ ከነዚህ መካከል ሬድዋን ናስር በራሱ ጎል ላይ ያስቆጠረው ነው።

– አቡበከር ናስር በሦስት ጎሎች በርካታ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች ሲሆን መስፍን ታፈሰ እና ሙጂብ ቃሲም ሁለት አስቆጥረዋል።

– በተቆጠሩ አስራ ሰባት ጎሎች ላይ ዘጠኝ ተጫዋቾች በማመቻቸት ረገድ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል።

– ዳንኤል ደርቤ እና ብሩክ በየነ ጎል በማስቆጠር እና ለጎል በማመቻቸት ጥሩ ሳምነት ያሳለፉ ተጫዋቾች ናቸው።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት 25 ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ ተመዝግቧል።

– የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ በዚህ ሳምንት የቀይ ካርድ የተመለከተ ብቸኛው ተጫዋች ነው።

– አምስት ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ የተመዘዘበት የጊዮርጊስ እና ቡና ጨዋታ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

– ጅማ አባ ጅፋር አራት የማስጠንቀቂያ ካርድ በመመልከት የሳምንቱን ከፍተኛ ቁጥር ይዟል።

– ሰበታ፣ ድቻ፣ ሀዋሳ እና ሆሳዕና አንድ ቢጫ ካርድ ብቻ የተመለከቱ ቡድኖች ናቸው።

ዕውነታዎች

– አቡበከር ናስር በፕሪምየር ሊጉ የሸገር ደርቢ ጨዋታዎች ላይ ሐት-ትሪክ የሰራ የመጀመርያው ተጫዋች ሆኗል።

– የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው በተከታታይ አራት ጨዋታዎች በጎል ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። (ጎል – አሲስት – ጎል+አሲስት – አሲስት)

– አቡበከር ናስር አምበልነት እና ሐት-ትሪክ ተገጣጥመውለታል። የቡድኑ ሁለተኛ አምበል የሆነው አቡበከር አምና ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ ገብቶ ስሑል ሽረ ላይ ሦስት ጎሎች ማስቆጠሩ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮም ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሐት-ትሪክ ሲሰራ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ነበር።

– በዚህ ሳምንት ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች መክነዋል። ይህም የዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ነው። ፀጋዬ ብርሀኑ በሜንሳህ ሶሆሆ ሲመለስበት አቡበከር ናስር ወደ ውጪ ሰዶታል።

– ሶሆሆ ሜንሳህ የፀጋዬ ብርሀኑን የመጀመርያ እና በድጋሚ የተመታ ፍፁም ቅጣትን አድኗል። ይህ ሲከሰትም ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

– የዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ የአዲስ አበባ ስታዲየም የመክፈቻ እና መዝጊያ በአቻ ውጤት ሆኗል። በመክፈቻው ሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ያለ ጎል አቻ ሲለያዩ በመዝጊያው ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና አንድ አቻ ተለያይተዋል።

– ኢትዮጵያ ቡና በሸገር ደርቢ ድል ሲያስመዘግብ ከ2009 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው። በ2009 በኢኮ ፊቨ ጎል 1-0 ካሸነፈ በኋላ አራት አቻ ተለያይቶ ሁለት ተሸንፏል። (የዓምናውን ጨምሮ)

– ሀዲያ ሆሳዕና በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ ጥሏል። አራት ተከታታይ የመክፈቻ ጨዋታዎች ያደረገው ቡድኑ ከወልቂጤ ነጥብ ቢጋራም እስካሁን ያልተሸነፈው ብቸኛ ቡድን ነው።

– ሙጂብ ቃሲም በጭማሪ ደቂቃ የተስማማው ይመስላል። በዚህ ሳምንት ፋሲል ሲዳማን 2-0 ሲያሸንፍ አጥቂው በመጀመርያው አጋማሽ ሦስተኛ የጭማሪ ደቂቃ እና በሁለተኛው አጋማሽ ሦስተኛ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ጎል አስቆጥሯል።

– የሸገር ደርቢ ለፓትሪክ ማታሲ አልሆነውም። ኬንያዊው ግብ ጠባቂ በ2011 በቀየሰ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ የነበረ ሲሆን ዘንድሮም ይህን ደግሞታል። አስገራሚው ነገር ሁለቱንም ጥፋት የፈፀመው በአቡበከር ላይ የነበረ ሲሆን ካርዱን የመዘዙበትም ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ናቸው።

– ወላይታ ድቻ አራተኛ ተከታታይ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ይህም ከሊጉ ቡድኖች ቀዳሚ ያደርገዋል።

– አዲስ አበባ ስታዲየም 36 ጨዋታዎች ተከናውነውበት ለተከታዩ አስተናጋጅ ጅማ ስታዲየም ሊጉን አስረክቧል። አንጋፋው ስታዲየም አዲስ ነገር ተፈጥሮ ጨዋታዎች ወደ አዲስ አበባ ካልመጡ በቀር ዘንድሮ ተጨማሪ የሊግ ጨዋታ የማይከናወንበት ሲሆን ይህም ሊጉ ከ1991 በኋላ በሜዳው ላይ ዝቅተኛ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ያስተናገደበት ዓመት ያርገዋል። በ1990 በአዲስ አበባ ስታዲየም 28 ጨዋታዎች ሲደረጉ በ1991 እንዳሁኑ በተመሳሳይ 36 ጨዋታዎች ተደርገውበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ