ሴቶች ፕሪምየር ሊገ | የንግድ ባንክ እና መከላከያ ጨዋታ በአወዛጋቢ ክስተት ተቋረጠ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመከላከያ አገናኝቶ የነበረ ሲሆን በ83ኛው ደቂቃ ላይ በተፈጠረ አወዛጋቢ ክስተት ለመቋረጥ ተገዷል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ቀን በ10:00 በመከላከያ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል መደረግ ጀምሯል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ 4ኛውደቂቃ ላይ መዲና ዐወል ከኤደን ሺፈራው የተሻገረላትን ኳስ በድንቅ አጨራረስ የንግድ ባንኳን ግብ ጠባቂ ንግስቲ መዐዛን ስህተት ተጠቅማ በማስቆጠር መከላከያን መሪ አድርጋለች፡፡

ንግድ ባንኮች አቻ ለመሆን በገነሜ ወርቁ እና ሎዛ አበራ የርቀት ሙከራዎችን ቢያደርጉም የግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና እና የግቡ ቋሚ ብረት በተደጋጋሚ ሲያከሽፉባቸው ተስተውሏል፡፡ ሆኖም 31ኛው ደቂቃ አማካይዋ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ከኤደን ሺፈራው ጋር ተጋጭታ በጉልበቷ ላይ በደረሰባት ጉዳት በአምቡላንስ ወደ አላቲዮን ሆስፒታል አምርታለች፡፡ ተጫዋቿን ተክታ አረጋሽ ካልሳ ወደ ሜዳ ከገባች በኃላ በተደጋጋሚ ጫና መፍጠር ችለዋል። በተለይ አረጋሽ በግራ በኩል አክርራ መታ ብረት የመለሰባት አስቆጪ ሙከራ ነበረች፡፡

ከእረፍት መልስ ባማረ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የቀጠለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በተጋጋለ የሜዳ ላይ ተነሳሽነት የቀጠለ ሲሆንም መከላከያ በመዲና ዐወል እና ሴናፍ ዋቁማ፤ ንግድ ባንክ በገነሜ የቅጣት ምት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን 59ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች አቻ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ረሂማ ዘርጋው ከቀኝ በኩል ወደ ግብ ክልል የላከቻት ኳስ አረጋሽ ካልሳ ጋር ደርሶ ወደ ጎልነት ለውጣው ክለቧን አቻ አድርጋለች፡፡

ጨዋታው በዚህ መልኩ ቀጥሎ 83ኛው ደቂቃ ላይ አወዛጋቢ ክስተት ተከስቶ ለመቋረጥ ተገዷል፡፡ በዚህኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለ ላይ ከሳጥን ውጪ ኤደን ሺፈራው ጥፋት ሰርታለች በሚል የዕለቱ ዋና ዳኛ ፀሀይ መላኩ ጥፋት ተፈፅሟል በማለት የቅጣት ምት ሰጥተዋል፡፡ ቅጣት ምቱንም ሎዛ አበራ አክርራ መታ የግቡን የላይኛው ቋሚ ነክቶ ከሜዳው አካል ጋር ተጋጭቶ ወደ ሲመለስ የዕለቱ ዋና ዳኛ ፀሀይ ጥፋት ተፈፅሟል ብላ ለመከላከያ የመልስ ምት በሰጠችበት ቅፅበት ረዳት ዳኛዋ ወይንሸት አበራ ኳሱ መስመር አልፏል በሚል የእጅ ባንዲራዋን በማውለብለብ ጎል መሆኑን ለዳኛዋ አስረድታ ጎል ሆኖ ፀድቋል።

ውሳኔውን ያልተቀበሉት የመከላከያ ተጫዋቾች ከዳኞች ጋር በፈጠሩት ክርክር በእንባ ታጅበው ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል፡፡ በዕለቱም የመከላከያ ክለብ ከፍተኛ አመራሮች እና አሰልጣኞች “ጨዋታው አይደረግም። እንዲህ እየተበደልን ጨዋታ የማድረግ ሞራሉ የለንም። በማለት ሜዳውን ለቀው የሄዱ ሲሆን ከዚህ ሁነት በኃላ የመከላከያ ክለብ ጨዋታውን እያስቀረፁ ስለነበር ለዕለቱ ኮሚሽነር የጨዋታውን ቪዲዮ ካሴት በመስጠት እንዲሁም በአምበሏ ፅዮን አማካኝነት ክስ አስመዝግበው ጨዋታው 2 ለ 1 ሆኖ ተቋርጧል፡፡

የመሐል ዳኛዋ ፀሀይ መላኩ በሜዳ ላይ የነበሩት የንግድ ባንክ ተጫዋቾች ያሰናበተች ሲሆን በቀጣይ ቀንም የዚህ ጨዋታ ውሳኔ የውድድር ስነ ስርአት ኮሚቴ በደብዳቤ ይገልፃል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ