ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ6ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ጀማል ጣሰው – ወልቂጤ ከተማ

ጀማል ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በነበረው ጨዋታ ሦስት የሚደርሱ አደገኛ ሙከራዎችን ከመመለሱ ባሻገር ከግብ ክልሉ ወጣ ብሎ ረዝመው የሚመጡ ኳሶችን በማጥራት ተጨማሪ ጥቃቶችን አክሽፏል። ከዚህም ባሻገር ግብ ካስተናገዱ በኋላ የቡድን ጓደኞቹ ስሜታዊ በሆኑባቸው ደቂቃዎች ልምዱን በሚመጥን ሁኔታ ቡድኑን በማረጋጋት ካላስፈላጊ ኪሳራ ታድጓቸዋል።

ተከላካዮች

ዳንኤል ደርቤ – ሀዋሳ ከተማ

ከሁለት ሳምንታት በኃላ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ተመልሶ በመስመር ተመላላሽነት ሚና ድንቅ የጨዋታ ጊዜ ያሳለፈው ዳንኤል የቡድኑን የቀኝ መስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ አስፈሪ እንዲሆን አድርጓል። በጨዋታውም አንድ ግብ ሲያስቆጥር ለቡድኑን አራተኛ የነበረችውን የመስፍን ታፈሰ ጎልም ማመቻቸት ችሏል።

ዳግም ንጉሤ – ወልቂጤ ከተማ

ከጉዳት መልስ ቡድኑን ደግም ማገልገል የቻለው ዳግም ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ ሲከላከል በነበረው የወልቂጤ የኋላ ክፍል ጀርባ ከሚጣሉ ኳሶች አደጋ እንዳይፈጠር በማድረግ እንዲሁም ፈጣኖቹን የሆሳዕና አጥቂዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በመቆጣጠር መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል።

መላኩ ወልዴ – ጅማ አባ ጅፋር

ወደ ራሱ ሜዳ አፈግፍጎ ይከላከል በነበረው የጅማ አባ ጅፋር የተከላካይ መስመር ውስጥ የመከላከል አደረጃጀቱን ይመራበት የነበረው መንገድ እና የሰበታን ወሳኝ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ያቋረጠባቸው ሒደቶች እንዲሁም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የነበረው የበላይነት በሳምንቱ ምርጥ ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ደስታ ዮሐንስ – ሀዋሳ ከተማ

ብርታት በሚጠይቀው የመስመር ተመላላሽነት ሚና የነበረው ደስታ ልክ እንደ ዳንኤል ሁሉ ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ በማድረግ እና በተሻጋሪ ኳሶቹም ጭምር በመታገዝ የሀዋሳን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያግዝ ውሏል። ሀዋሳ በብሩክ በየነ አማካይነት ሦስተኛውን ግብ ሲያስቆጥር አመቻችቶ ያቀበለው ደስታ ዮሐንስ ነበር

አማካዮች

ዳዊት ታደሰ – ሀዋሳ ከተማ

በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀዳሚው የቡድኑ አሰላለፍ ውስጥ የተካተተው ዳዊት የጊዮርጊሱን መጥፎ ትውስታ የሚያስረሳ ጨዋታ አከናውኗል። ጉዳት የገጠመው ጋብርኤል አህመድን ቦታ በአግባቡ በመሸፈንም የድቻን አማካዮች እንቅስቃሴ በመገደብ ቡድኑ ያለስጋት ማጥቃት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ እንዲኖረው የበኩሉን ተወጥቷል።

አማኑኤል ጎበና – ሀዲያ ሆሳዕና

ታታሪው አማካይ ሰፊ ሜዳ አካሎ የመጫወት ልማዱን ያሳየበትን ጨዋታ አስመልክቶናል። በማጥቃት እና በመከላከሉ ረገድ መሀል ላይ ሁለት አማካዮችን ለተጠቀመው ቡድን ሚዛን አጠባበቅ ጉልህ ድርሻ የነበረው የነበረው አማኑኤል ከተስፋዬ አለባቸው ጋር ጥሩ ጥምረት በማሳየት መልሶ ማጥቃትን አልሞ ለገባው ሆሳዕና የማጥቃት ሽግግሮችን በማፋፋም የድርሻውን ተወጥቷል።

ታፈሰ ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

እጅግ አስገራሚ ለውጥ እየታየበት ያለው ታፈሰ ሰለሞን በአምስተኛው ሳምንት ምርጣችን ውስጥ ያስገባውን ብቃት በመድገም በሸገር ደርቢ ላይም ጎልቶ መውጣት ችሏል። አማካይ ክፍሉን በታታሪነት ሲመራ የዋለው ታፈሰ ለቀዳሚው ፍፁም ቅጣት ምት መንስዔ ለነበረው እንቅስቃሴ እንዲሁም ለሁለተኛው ግብ መነሻ የነበረውን ኳስ በጊዮርጊስ ተከላካዮች መሐል በመሰንጠቅ አጥቂዎችን ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቷል። ወደ ኃላ ተስቦ ኳስ በማደራጀትም ቡድኑ እስከመጨረሻው ድረስ ሲፈልገው የነበረውን ክፍተት ለማስገኘት ብዙ ለፍቷል።

አጥቂዎች

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

በሸገር ደርቢ የመጀመሪያ ግቡን ከማስቆጠር አልፎ ሐት-ትሪክ የሰራው አቡበከር በጨዋታው ሁሉም ነገር ውስጥ ነበረበት። በፍጥነቱ የጊዮርጊስን ተከላካዮች ሲረብሽ የዋለው አቡበከር ለሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች መገኘት ምክንያት መሆን ከመቻሉ ባሻገር እንደ አምበል ቡድኑን በማነሳሳት ኃላፊነቱን ሲወጣ በመዋሉ ለሦስተኛ ጊዜ የምርጥ ቡድናችን አባል አድርገነዋል።

መስፍን ታፈሰ – ሀዋሳ ከተማ

ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ከጉዳቱ አገግሞ ሀዋሳ ከተማን ማገልገል የቻለው መስፍን ስለምን ቀጣዩ ትልቅ ተጫዋች ለመሆን እንደሚጠበቅ አሳይቷል። ግዙፉ አጥቂ ከብሩክ በየነ ጋር ድንቅ ጥምረት በማሳየት እንዲሁም ጉልበት እና ፍጥነቱን በመጠቀም ለድቻ ተከላካዮች እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ በዋለበት ጨዋታ ሁለት ኳሶችን ከማረብ ማገናኘት ችሏል።

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

ሙጂብ በየጨዋታ ሳምንቱ ለፋሲል ግብ ማምረቱን ቀጥሏል። በተለይም ከቆሙ ካሶች መነሻነት ካልሆነ በቀር በርካታ የግብ ዕድሎን እየፈጠረ ባልሆነው ቡድን ውስጥ ሙጂብ ያገኛቸውን ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም በወሳኝ ደቂቃዎች ላይ ለቡድኑ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ለሁለተኛ ጊዜ የድረ-ገፃችንን ምርጥ ቡድን በአጥቂነት እንዲመራ ሆኗል።

አሰልጣኝ

ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ውድድሩ ሲጀምር ደካማ መዋቅር የነበረውን ቡድን በማሻሻል እና በአዕምሮ ረገድ ጠንክሮ እንዲመጣ በማድረግ አሰልጣኝ ሙሉጌታ በጉልህ የሚታይ ስራ ሰርቷል። በዚህ ሳምንት ወላይታ ድቻን ሲገጥም ባልተጠበቁ መልኩ የተጫዋቼች ለውጥ አድርጎ 3-5-2 አሰላለፍ ለጨዋታው በመቅረብ ከጨዋታ ብልጫ ጋር በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፎ መውጣት ችሏል።

ተጠባባቂዎች

ሶሆሆ ሜንሳህ – ሀዋሳ ከተማ
ከድር ኩሊባሊ – ፋሲል ከነማ
አህመድ ረሺድ – ባህር ዳር ከተማ
ተስፋዬ አለባቸው – ሀዲያ ሆሳዕና
ጋዲሳ መብራቴ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ