ሊዲያ ታፈሰ ብቸኛዋ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በመሐል ዳኝነት ግልጋሎት ለመስጠት ወደ ካሜሩን አምርታለች፡፡
የ2021 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ውድድር በካሜሩን አስተናጋጅነት ከጥር 8 እስከ 30 ድረስ በያውንዴ ከተማ ይደረጋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ወደ ውድድሩ የሚያመሩ ሲሆን በዓምላክ ተሰማ በVAR ዳኝነት ሊዲያ ታፈሰ ደግሞ በዋና ዳኝነት ወደ ስፍራው ያቀናሉ፡፡ የቻን ውድድርን ብቸኛዋ ሴት ዋና ዳኛ በመሆን የተመረጠችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ውድድሩ ወደ ወሚደረግበት ሀገር ያመራች ሲሆን ስለ ነበራት ዝግጅት እና ስለ እቅዷ ከጉዞዋ በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቧን ገልፃለች፡፡
“ራሴን በደንብ ቼክ ሳደርግ ነበር የቆየሁት። ዝግጅት እያደረኩ የነበረው ለቻኑ ብቻም ሳይሆን መጀመሪያም በኮቪድ ምክንያት ብዙም እረፍት አላደረኩም። ከውድድሮች መራቃችን ብዙ ተፅኖዎች አሉብን። ያው ሰውነታችን ላይ የሚያመጣብን ተፅዕኖዎች እንዳሉ ሆነው አሁን ደግሞ ውድድር ጫና ባለው ላይ ነው ያሳለፍኩት። ልምምድ እየሰራሁ ጨዋታም እያጫወትኩ ነበር፡፡ በተለይ ፕሪምየር ሊጉ መጀመሩ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሦስት ጨዋታዎችን መርቼ ነው የምሄደው። ልምምዴንም መስራት በሚገባኝ ልክ ሰርቻለሁፀ ከፈጣሪ ጋር ከእኔ አሁን እዛ በሄድኩ ሰአት የሚጠበቅበኝን ሁሉ መጀመሪያ የሚደረጉ ቴስተቶችን በአግባቡ መወጣት ወደ ውድድሩም ስገባ የተሰጠኝን ዕድል በአግባቡ መጠቀም አለብኝ ብዬ ነው የማስበው። እሱን በአግባቡ ከተወጣሁኝ ለሚቀጥሉት ውድድሮች ለእኔም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሴቶችም መንገድ የመክፈቱ ስራ ይጠበቅብኛል። ትልቅ ሀላፊነት ያለው ነገር ነው ተቀብዬ የምሄደው። እንደ ሀገር ኢትዮጵያን በመወከሌ፤ በተጨማሪ ከአፍሪካ አንዷ ሴት በመሆኔ ወደ ውድድሩ ስገባ ኢትዮጵያዊነቴም ስለሆነ የሚጠራው በዚህም ስም የበለጠ ለማኩራት ለሁላችሁም በዓለም ዋንጫ እንደተደሰታችሁኝ በዚህም የቻን ያገኘሁትን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ነው በደንብ የተዘጋጀውት። ሜንታሊም ፊዚካሊም ዝግጁ ነኝ። ከፈጣሪ ጋራ እንግዲህ የበለጠ በቦታው ተገኝቶ ያለውንም ነገር በደንብ ለማሳየት ነው ጥረቴ።” ስትል ተናግራለች፡፡
የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪምየር ሊግን እየመራች በውድድር ማሳለፏ እና ጠንከር ያለ አቅም በሚጠይቀው ቻን ውድድር ላይ በብቃት ለመዳኘት ምን ያህል ይጠቅመኛል ብለሽ ታስቢያለሽ ብለን ላነሳንላት ጥያቄ ስትመልስ “ጨዋታዎች ቢኖሩኝም በቀጣዮች ቀናት ልምምድ እሰራለሁ። አንዳንዴ የእኛ ሊግ ፈጣን አይደለም። ወጣ ገባ እያልንም ነው የምናጫውተው ጠንካራ ቢባልም እውነት ለመናገር ይሄን ያህል ፈታኝ የሆኑ ጨዋታዎችን ግን አላጫወትኩም። አቅሜንም በዛው ልክ ስለማየው ብዙም ይሄን ያህል እንደዚህ ከባድ ብዬ ፈትኖኛልም ብዬማስበው አይደለም። ያለ ሰዓት የምታጫውታቸው አሉ ለምሳሌ የቀን አራት ሰዓት ላይ ስታጫውት የመክበድ ነገር አለው። ትንሽ አየሩ ተፅዕኖ አለው። ወደ ውድድሩ ስትገባ አየራችን ለእኔ ይጠቅመኛል ብዬ አስባለሁ፤ ይቀላል ብዬ ገምታለሁ። የእኛ አየር በጣም ከባድ ነው፡፡ ልምምድ ስትሰራም ስታጫውትም ይጨንቃል። ብዙዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ምክንያት የሚያቀርቡት አየራችሁ ይከብዳል ነው የሚሉት። እና ይህን በማሰብ ልምምዶቼን ከበድ ባለ መልኩ ሰርቻለሁ፤ ብዙ ዳኛ ስለሚኖር። ከአንድ ወይም ከሁለት ጨዋታ በላይ ላትመራም ትችላለህ። እንደ ውድድሩ ሁኔታ VAR ስላለ ይሄን ያህል ይከብዱኛል ብዬ አልጠብቅም። በየትኛውም ሰአት VAR እንደሚጠቀሙ አልነገሩኝም። ግን ከዚህ ቀደም በዚህ ሒደት ስላጫወትኩኝ ይከብደኛል ብዬም አላስብም።”
© ሶከር ኢትዮጵያ