የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዙር መርሐ ግብር የት ይደረጋል የሚለው ጉዳይ በቅርቡ ይለይለታል

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዲቪዚዮን የሁለተኛው ዙር መርሀ ግብር በሚደረግበት ቦታ ዙርያ ዛሬ ውይይት ተደረገ፡፡

በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ቀደም ብሎ በሀዋሳ ይደረጋል በተባለው መሠረት ውድድሩ እየተደረገ ሰባተኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰ ሲሆን የሁለተኛው ዙር ውድድር በአዳማ ከተማ እንዲደረግ አስቀድሞ መርሀ ግብር የወጣለት ቢሆንም የቦታ ለውጥ ሊኖረው እንደሚችል በዛሬው ዕለት ክለቦች ከውድድሩ መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡

ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ በሀዋሳ ሰው የሰው ሰራሽ ሳር ሜዳ ላይ በነበረው ውይይት ላይ ክለቦች የሁለተኛውም ዙር በሀዋሳ እንዲደረግ ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም ” የመጫወቻ ሜዳው አርቴፊሻል በመሆኑ ተጫዋቾችን ለጉዳት እየዳረገ ነው። ስለዚህ የተፈጥሮ ሳር ሜዳ ስለሚያስፈልግ መቀየር አለበት።” የሚል ሀሳብ የተነሳ ሲሆን በአማራጭነትም ሁለተኛው ዙር በአዳማ አልያም አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ ክለቦች በመጫወቻ ሳሩ ቅሬታ ቢያሰሙም የኮቪድ ምርመራን በሲዳማ ክልል አማካኝነት በነጻ እየተመረመሩ እስካሁን በመዝለቃቸው ወጪያቸውን የተቀነሰላቸው በመሆኑ ውድድሩ ወደ ሌላ ከተማ ከተለወጠ ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት ስለሚገደዱ ከሀዋሳ ወደ ሌላ ከተማ ውድድሩ ከሄደ ቡድኖች ከፋይናንስ አወጣጥ ጋር ችግር ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ ሊፈጠር ስለሚችል በሌላ በኩል ክለቦችን ያሳሰበ ጉዳይ እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

የካቲት 6 እንደሚጀመር የሚጠበቀው የሁለተኛው ዙር የሊጉ መርሀ ግብር የት ይደረጋል ለሚለው በስብሰባው ምንም ውሳኔ ያልተሰጠበት ሲሆን ክለቦች በአጭር ቀን ውስጥ ተነጋግረው መልስ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ጥር 21 የሚጠናቀቀው የአንደኛው ዙር ውድድር የአስራ አምስት ቀናት እረፍትን ለክለቦች ከሰጠ በኃላ በየካቲት 6 በቀጣይ በሚገለፀው ከተማ የሚጀመር ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ