የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር በሀዋሳ እንደቀጠለ ነው፡፡ ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አንደኛ እና ሁለተኛ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማን በሰባተኛ ሳምንት ተጠባቂ በነበረ መርሀ ግብር አገናኝቶ ባንክ 4 ለ 0 በማሸነፍ የድል ጉዞውን አስቀጥሏል፡፡
ከአንድ ዓመት በኃላ ከማልታው ክለብ ቢርኪርካራ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ለንግድ ባንክ በከፍተኛ ወርሀዊ ክፍያ በመፈረም ለክለቡ ግልጋሎት እየሰጠች የምትገኘው ሎዛ እስከ ቅርብ ሳምንታት የቀደመው አቅሟ ላይ መገኘት ባትችልም ዛሬ ግን ንግድ ባንክ ባሸነፈበት ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴን ከማድረጓ ባሻገር ሁለት ጎሩም ኳሶችን ለቡድኗ አስቆጥራ ወጥታለች።
በሒደት ወደቀደመ አቋሟ እየተመለሰች የምትገኘው አጥቂዋ ሎዛ አበራ ከዛሬው ጨዋታ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስላሳየችው ብቃት እንዲሁም ስለዚህ ዓመት የራሷ እና የክለቧ እቅድ አጭር ቆይታን አድርጋለች፡፡
“አንዳንድ ጊዜ ወደ አዲስ ቡድን ስትመጣ ነገሮች መጀመሪያ ላይ ትንሽ ሊከብዱህ ይችላሉ። ግን እስክትግባባ ድረስ ነው፡፡ እግር ኳስ ደግሞ በራሱ ቋንቋ ስለሆነ በሒደት መግባባት ችለኛል። አቅሜንም ለማሳየት እየሞከርኩ ነው፡፡ እንደ ቡድን ጥሩ መሆናችን እኔንም ጎልቼ እንድወጣ አስችሎኛል ብዬ አስባለሁ።
“ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቅ ቡድን ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ቡድን ጋር ሻምፒዮን ለመሆን እና ቀጥሎ በአፍሪካ ያሉትን ውድድሮች የተሳካ ለማድረግ ነው፡፡ ጥሩ የውድድር ዓመት እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ በእርግጠኝነት ጎል አስቆጣሪ እንደምሆን አምናለሁ። ውድድሩን ከጀመርን ጊዜ ጀምሮ አላማዬም እቅዴም ያ ነው፡፡ጎል አስቆጣሪ ተጫዋች እንደመሆኔ መጠን መጀመሪያ ክለቡ የተሻለ ውጤት ካመጣ እኔ ኮከብ ተጫዋች የማልሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህ በዚህም ዓመት የተሻለ ጎሎችን አስቆጥሬ እንደ ቡድንም ሻምፒዮን ሆነን ኮከብ አግቢ ለመሆን ነው ዕቅዴ፡፡
“የቡድናችንን ጥንካሬ ዛሬ በደንብ አሳይተናል ብዬ አስባለሁ። ትልቅ ቡድን እንደሆነ አሳይተናል። ትልቅ ጨዋታ ነበር ዛሬ። ሁሉም ልጆች በየቦታቸው ጥሩ ነበሩ። ቡድኑ በአሸናፊነት እየሄደ መሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው ብዬ አስባለሁ።”
ሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ቀናት በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ልዩነት ፈጣሪ የሆኑ ተጫዋቾችን ወደ አንባቢዎቿ እንደምታቀርብ ከወዲሁ እንገልፃለን፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ