ሰበታ በክረምቱ ካስፈረመው ተጫዋች ጋር ሲለያይ የአዲስ ተጫዋች ውል አስፀድቋል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን ባለው ጅማሮ ወጣ ገባ የሆነ አቋም እያሳየ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከአንድ ተጫዋቹ ጋር ሲለያይ የአንድ ተጫዋች ውል አስፀድቋል።

በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እየተመራ እስከ ስድስተኛ ሳምንት ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሁለት ጨዋታ ድል ቀንቶት በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ ጨዋታ አቻ የተለያየው ሰበታ ከተማ በቅድመ ዝግጅት ወቅት ለቡድኑ ከፈረሙ ተጫዋች መካከል አንዱ የነበረው የቀድሞ የመከላከያ የመስመር ተከላካይ ሙሉቀን ደሳለኝ ለቡድኑ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረ ቢሆንም በስምምነት ከሰበታ ጋር መለያየታቸው ተሰምቷል።

አስቀድሞ እንደፈረመ ቢነገርም ውሉ ባለመፅደቁ ምክንያት እስካሁን ሳይጫወት የቀረው ከኢትዮጵያ ቡና ታዳጊን ቡድን አንስቶ በደደቢት የተጫወተውና በክረምቱ ወደ ወልዋሎ አምርቶ የነበረው ወጣቱ የተከላካይ አማካይ አብዱልባሲጥ ከማል በዛሬው ዕለት ዝውውሩ በፌዴሬሽን ፀድቆለታል።

አብዱልባሲጥ ለሰበታ ለመጫወት ውሉ መፅደቁን ተከትሎ በቦታው ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ