“ይህ በዚህ መልኩ አይቀጥልም፤ የፋሲል አስፈሪነት ይመለሳል” አምሳሉ ጥላሁን

እስከ ስድስተኛው ሳምንት ባለው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለፋሲል ከነማ መልካም ጉዞ ጎል ማስቆጠረረም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ከሚገኘው አምሳሉ ጥላሁን ጋር ቆይታ አድርገናል።

ከዳሽን ቢራ ተለያይቶ ዐፄዎቹን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ቡድኑ ውስጥ ቁልፍ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል ይመደባል። ልባሙ ተጫዋች በመከላከል እና በማጥቃት ሽግግር ውስጥ ጥሩ ተሳትፎ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ ከመሆኑ ባሻገር ከቅጣት ምት ኳሶች ጎል በማስቆጠር ይታወቃል። በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እስከ ስድስተኛ ሳምንት የፋሲል ከነማ መልካም ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው አምሳሉ ከኳስ ውጭ ሜዳ ውስጥ ቡድኑን የሚመራበት እና የሚያነቃቃበት ሁኔታ ደግሞ በቡድኑ ውስጥ የተለየ ተጫዋች እያደረገው መጥቷል። ቡድናቸው እስካሁን የመጣበት ጉዞ እና በቀጣይ መደረግ አለባቸው ብሎ ስለሚያስበው ነገር ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አሰናድተነዋል።

“የዘንድሮ ውድድር ለእኛ ቡድን በተለይ በጣም ከብዶናል። ያለውን ነገር መልመድ አልቻልንም። ለምሳሌ የእኛ ቡድን የደጋፊ ቡድን ነው። ደጋፊዎቻችን ከተጫዋች በላይ የሚቆሙበት ቡድን ነው። ደጋፊዎች ብዙ ነገር የሚጠብቁበት ቡድን ነው። እስካሁን ባለው ነገር አስፈሪነታችንን ይዘን ባለመቅረባችን ውድድሩን ከባድ አድርጎብናል። ለኔም ከባለፉት ዓመታት እንደ ዘንድሮ ውድድር በግሌ የከበደኝ ዓመት የለም። እስከ ስድስተኛው ሳምንት ድረስ ቡድናችን ዛሬ ነገ እያልን ልናስተካክለው አልቻልንም። አስፈሪነታችን አልተመለሰም። በዚህ ምክንያት ጫና እና ጭንቀት ውስጥ ገብተናል። ምክንያቱ ደግሞ ሜዳ ውስጥ የሚታይ ነገር ነው። ፋሲልን ወደ አስፈሪነቱ ማምጣት ስለምንፈልግ ከጉጉት የተነሳ ሳናውቀው ራሳችንን ጫና ውስጥ ከተነዋል። ይህን ለማስተካከል በጣም በብዙ መንገድ እየሞከርን ነው። ለፋሲል ከዚህ የተሻለ ውጤት ማምጣት እናስባለን። እስካሁን ባደረግነው ጨዋታ ነጥብ የጣልንባቸው ጨዋታዎች ወደ ኃላ ዞር ብለን ስናስበው ትንሽ የሚነካህ ነገር አለ። ማምጣት እየቻልን ያላመጣነው ነገር አለ። ይህ በዚህ መልኩ አይቀጥልም። የፋሲል አስፈሪነት ይመለሳል። ይህን ለማምጣት በጣም እየለፋን ነው። ደጋፊው ከእኛ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ። የድሮ ፋሲል እንዲመጣ ስለምፈልግ ነው ሜዳ ውስጥ የምጮኸው የምናገረው የቡድንድ አጋሮቼን የማነሳሳው።

“በእኔ የእግርኳስ ታሪክ ፋሲል ከነማ የሊጉ ሻምፒዮን እንዲሆን አስባለው። ይህንንም ማድረግ የሚያስችል በቂ ስብስብና አቅም አለን ብዬ አስባለሁ። ውስጣችን ጉጉት አለ። ይህን ክለብ ታላቅ ለማድረግ እና ደጋፊውን ለማስደሰት እንፈልጋለን። ከዚህ በኃላ ያሉ ሁሉም ጨዋታዎች ለእኛ አንድ ዐይነት ነው። እከሌ ክለብ ብለን የምንመርጠው የለም። የኢትዮጵያ እግርኳስ አንድ ዐይነት ነው። በጊዜው እና በዘጠና ደቂቃ የጨዋታ እንቅስቃሴ የምታሳየው አቋም ነው ውጤት ይዘህ የምትወጣው። ስለዚህ ለዚህ ክለብ ብለን የተለየ ግምት ሳንሰጥ ከዚህ በኃላ ያሉትን ጨዋታዎች በትኩረት በመጫወት ወደምንፈልገው ውጤት እናመራለን ብዬ አስባለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ