መቀመጫቸውን የትግራይ ክልል ባደረጉ ክለቦች ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ልዩ የዝውውር ጊዜ ቢዘጋጅም ውሳኔው የተጫዋቾችን ጥቅም ያላገናዘበ እንደሆነ ተጫዋቾቹ ቅሬታቸውን ገሎፀዋል።
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ምክንያት መቀመጫቸውን ትግራይ ክልል ያደረጉ ሦስቱ ክለቦች ከውድድር ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ የተጫዋቾቹ ከቀጣይ ዕጣ ፈንታ አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል። በተለይ ችግሩ ከተፈጠረበት ቦታ ዘግይተው የመጡ ተጫዋቾች ሁሉም ክለቦች በወጣው የዝውውር ጊዜ ተጠቅመው የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች አስፈርመው ካጠናቀቁ በኃላ የመጡ መሆናቸው ችግራቸውን የበለጠ አስፍቶታል። በዚህም መነሻነት የተለየ ዝውውር መስኮት እንዲመቻችላቸው ለፌዴሬሽኑን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመጀመርያ ከታኅሣሥ 26 እስከ ታህሳስ 30/2013 ልዩ የዝውውር ጊዜ ለአምስት የስራ ቀናት አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ጊዜው በቂ አይደለም በሚል በድጋሚ ቀናቶችን በመጨመር እስከ እስከ ዛሬ ጥር 3 ቀን 11:00 ድረስ ማራዘሙን ይታወቃል።
ፌዴሬሽኑ የወሰነው እና ያስቀመጠው ልዩ የዝውውር ሒደት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጥቅማቸውን ያላገናዘበ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት አንደኛ አብዛኛው ክለቦች በተቀመጠው የተጫዋች ደንብ መሠረት ኮታቸው የሞላ መሆኑ ምንም እንኳ ልዩ የዝውውር መስኮት ቢከፈት የትም ክለብ ሄደው መጫወት የማይችሉበት ሁኔታ እንዳለ ይናገራሉ። “መሆን የነበረበት ክለቦች ተጨማሪ ኮታ ተፈቅዶላቸው እኛን የሚያስፈርሙበት ሁኔታ መፍጠር እንጂ ፌዴሬሽኑ ልዩ የዝውውር ጊዜን ፈቀድኩ ከማለት ውጭ ምንም ትርጉም የሌለው የኛን ወቅታዊ የችግር ሁኔታ ያላገናዘበ ውሳኔ ነው” ሲሉ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ቀድሞ በነበሩበት ክለብ ያልተከፈላቸው የአምስት ወር ደሞዝ በምን ሁኔታ እንደሚከፈላቸው አለማወቃቸው አሳሳቢ መሆኑን ገልፀዋል።
ዐወት ገብረሚካኤል፣ አክሊሉ አያናው፣ ሽመልስ ተገኝ፣ ዐመለ ሚልኪያስ፣ አስናቀ ሞገስ፣ ወንድወን አሸናፊ፣ አክሊሉ ዋለልኝ፣ ሄኖክ ገምቴሳ እና ሌሎች ተጫዋቾች ተጨምሮበት በቀረበው በዚህ የቅሬታ ሀሳብ “በአጠቃላይ ውድድሩ በችኮላ እኛን ታሳቢ ሳያደርግ መጀመሩ በብዙ መልኩ እኛ ዘግይተን የመጣን ተጫዋቾችን ጎድቷል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ አሁንም ቢሆን ወደ ተለያዩ ክለቦች የምናመራበት መንገድ እና ያልተከፈለን የአምስት ወር ደሞዝ የሚከፈለንበት ሁኔታ እንዲያመቻች።” ሲሉ ጠይቀዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማኅበር የተጫዋቾችን ጥቅም ለማስጠበቅ እስካሁን እየተንቀሳቀሰ ባይሆንም በቀጣይ ቀናት ድምጹን እንደሚያሰማ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ