የከፍተኛ ሊግ መረጃዎች እና የትኩረት ነጥቦች

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን በተለያዩ ከተሞች እየተደረጉ ይገኛሉ። በዚህ ውድድር ላይ የተመለከትናቸውን ዋና ዋና ነጥቦችን በምናቀርብበት ሳምንታዊው የትኩረት ዝግጅታችን ከመረጃዎች ጋር እንዲህ ቃኝተናል።
መርሐ ግብር ለውጥ

በቅድሚያ በወጣውና ለክለቦች እንዲሁም ለሚዲያ የተበተነው የከፍተኛ ሊጉ መርሐ ግብር የምድብ ሀ ለውጥ ማድረጉ ታውቋል። አስቀድሞ ሰኞ (4 እና 9) እና ማክሰኞ (4እና9) እንደሚካሄዱ ቢያሳይም የጥምቀት በዓል በመሁኑ ወደ ረቡዕ ለማካሄድ የታሰበ ሲሆን በዚህም

ረቡዕ ጥር 12/2013

ፌዴራል ፖሊስ 3:00 ለገጣፎ ለገዳዲ
ወልድያ ከተማ 5:00 ሰ|ሸ|ደ|ብርሃን
ደሴ ከተማ 8:00 ገላን ከተማ
ወሎ ኮምበልቻ 10:00 መከላከያ

ውይይት

የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል ተዘዋውሮ ቡድኖቹን እያወያየ ይገኛል። በሦስት ከተሞች ተከፋፍሎ የሚደረገው ይህው ውድድር በተመለከተ የከፍተኛ ሊግ ዋና ሰብሳቢ ዓሊሚራ መሐመድ እንዲሁም ምክትል ሰብሳዪ ሻምበል ሀለፎም በሦስቱም ከተሞች በመዘዋወር ከቡድኖች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በዋነኝነት ከተዋያዩባቸው ነጥቦች መካከል ቡድኖች ከጨዋታዎች 72 ሰዓት በፊት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በማድረግ ውጤቱን ማሳወቅ እንደሚገባቸው ደንቡ ላይ በተቀመጠው መሠረት ክለቦች ተጫዋቾች በማስመርመር ውጤታቸውን ቢያሳውቁም ተጫዋቾቻቸውን በመቆጣጠር ረገድ ግን ክፍተቶች መታየታቸውን ተከትሎ ምርመራ የተደረገላቸው ተጫዋቾች በተወሰነ ስፍራ ላይ ተለይተው እንዲቆዩ ካልተደረገ ቡድኑ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚተለልፈበት አፅንኦት ተሰጥቶታል።

ዳኝነት እና ከፍተኛ ሊግ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድሩ በራሱ ከፍ ያለ ጫና እና ውጥረት የተሞላበት መሆኑ ለዳኞች ጨዋታዎችን ከባድ ሲያደርግባቸው ይስተዋላል። በዘንድሮ ውድድር ዓመት ከአንደኛ ሊግ ያደጉት ዳኞች ከፍተኛ ሊግ ጨዋታ እየመሩ የሚገኝ ሲሆን በሶስቱም ከተሞች በተለይም በምድብ ለ እና ሐ ላይ ቡድኖች ከፍተኛ ቅሬታ እያሰሙ ይገኛል። በቦታው ያሉ አወዳዳሪ አካላት በቅርብ ሆነው ችግሩን እንዲፈቱ እንዲሁም የዳኞች ኮሜቴውም ጆሮ ሰጥቶ እንዲሰማ ያስፈልጋል።

በድጋሚ የተዋቀረው ኮሚቴ

በ2013 ውድድር ዓመት የምድብ ሐ ውድድር በድሬዳዋ ከተማ የሚካሄደውን የሚመሩት አብዛኛው የኮሚቴ አባላት በአዲስ ግለሰቦች መተካታቸው የታወቀ ሲሆን አወዳዳሪው አካል ከጅምሩ ጠንካራ ኮሚቴ አዋቅሮ አለመላኩ የሚያስወቅሰው ተግባር ቢሆንም ዘግይቶም ቢሆን ማስተካከያ ተደርጓል። አሁንም ቢሆን ግን የስራ ጫናዎች በድሬዳዋው ኮሚቴ ላይ ሊበዛ ስለሚችል አወዳዳሪው አካል ተጨማሪ ባለሙያተኛ ወደ ስፍራው በመላክ ውድድሩ በጥሩ ሁኔታ እንዲጓዝ ማድረግ ይኖርበታል።

ወንድምአገኝ ኪራን ተዋወቁት

በከፍተኛ ሊጉ አራት ጎሎች አስቆጥሮ ጎል አስቆጣሪነቱን እየመራ የሚገኘው ወንድማገኝ ኪራን እናስተዋውቃችሁ።

ስም፡ ወንድምአገኝ ኪራ
ቁመት፡ 1.71
ክብደት፡ 69 ኪ.ግ
ክለብ፡ ቤንች ማጂ ቡና
የሚጫወትበት ቦታ፡ አጥቂ

በቤንች ማጂ የተወለደው ወንድምአገኝ በሰፈሩ በሚገኘው ፕሮጀክት ላይ የጀመረው እንቅስቅሴ ከፍ ብሎ አንደኛ ሊግ በሚወዳደረው የከተማው ክለብ ቤንቺ ማጂ የእግርኳስ ህይወቱን በክለብ ደረጃ የጀመረ ሲሆን ቡድኑ ከአንደኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያድግ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

ወንድምአገኝ በከፍተኛ ሊጉ ዘንድሮ አራት ጎሎች ያስቆጠረ ሲሆን ጎል አስቆጣሪነትንም መምራት ጀምሯል። ተጫዋቹ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ሐት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች ሲሆን በውድድሩ መልካም እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ እና ቀጣይ እቅዱ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል። ” ከዚህ ቀደም በትውልድ ስፍራዬ ላለው ቤንች ማጂ ከአንደኛ ሊግ እስከ ከፍተኛ ሊግ ተጫውቻለሁ። ከዛም በከፋ ቡና እና ኢኮሥኮ የተጨወትኩ ሲሆን ወደ ቀድሞ ቡድኔ ተመልሻለሁ። አሁን ላለሁባት ደረጃ እንድደርስ የአሰልጣኙ እንዲሁም የወጌሻችን ጥላሁን ነጋሽ ምክሮች ረድተውኛል። ከዚህ በላይ እኔን የሚያስደስተኝ ቡድኔ ውጤታማ መሆኑ ነው። ቀጣይ ጠንክሬ በመሥራት ከዚህ በላይ ግቦችን ማስቆጠር ነው የምፈልገው። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ