የባህር ዳር እና ሀዋሳ ጨዋታ መጠናቀቁን ተከትሎ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ይህንን ብለዋል።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ
ስለጨዋታው
በመጀመሪያው ሰላሳ ደቂቃ በማስበው መልኩ ተጫዉተናል። ነገር ግን ጎል ካገባን በኃላ በተለይ በመጀመሪያው አርባ አምስት የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ወደ ኃላ ሸሽተናል። እንደዛም ሆኖ ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን የግብ ዕድሎች ብንጠቀም ኖሮ የተለየ የጨዋታ ውጤት ይኖር ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ በውጥረት የተሞላ ነበር ፤ ያልታሰበ ጎል ከርቀት ተመትቶ ነው የገባብን። ውጥረት የተሞላበት ስለነበር ልንተገብር ያሰብነውን ነገር ማድረግ አልቻልንም። ተጋጣሚያችን ሦስት ነጥብ አግኝቷል፤ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
የሀዋሳ አምስት አማካዮች መጠቀም ቡድኑን ክፍተት ያሳጣው ስለመሆኑ
በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ሰፋፊ ክፍተቶች ነበሩ። በቂ የመጫወቻ ሜዳ አግኝተናል። የግብ ዕድሎችንም መፍጠር ችለን ነበር ፤ ሆኖም ምንም አልተጠቀምንበትም። ምንም እንኳን የመስመር ተጫዋቾቼ እንደ ተመላላሽ (wing back) ቢሆኑም አጥቂዎቼ ከእነሱ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅሞች እያገኙ አልነበረም። ስለዚህ እዚህ ላይ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
በጨዋታው ቡድኑ ጥንቃቄን ስለመምረጡ
3-5-2 ስንጫወት የመስመር ተጫዋቾችን ለመጠቀም ፈልጌ ነበር። ቢሆንም የባህር ዳር ቡድን እንደተጀመረ የበላይነት ወስደውብን ስለነበር ተቸግረን ነበር። ከዛ ለመመለስ ያደረግነው ነገር ጥሩ ነበር። ሁሉም እስኪሞቃቸው ተቸግረን ነበር ከሞቁ በኋላ ደግሞ የተሻሉ ነበሩ። ግን ከእረፍት በኋላ ደግሞ አንድ ተከላካይ ቀንሰን ወደ 4-3-3 ገብተን ስለሚያስፈልገን ጎል አግብተን አሸንፈን ወጥተናል።
ስለኤፍሬም አሻሞ ቅያሪ
ያው የምንፈልገው ጎል አግብቶ ማሸነፍ ስለነበር ኤፍሬም ብቻ ሳይሄን ሌሎቹም አጋጣሙውን ካገኙ እንዲያገቡ ነው። ግን ዕድለኛ ሆኖ ደግሞ እሱ አግብቷል። በጣም ጥሩ ነበር ብዬ ነው የማስበው በዕለቱ ዛሬ።
© ሶከር ኢትዮጵያ