የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 3-1 ድሬዳዋ ከተማ

ከአመሻሹ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ዘርዓይ እና አሰልጣኝ ፍሰሀ ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።


አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

በቶሎ ወደ ጨዋታው ስለመመለሳቸው

የሚገርመው ተነጋግረን ነበር። ‘ግብ ቀድሞ እንኳን ቢቆጠርብን ከዚህ በፊት እንደነበረው መውረድ የለብንም። ምክንያቱም ዛሬ ሀዋሳ ከተማ ትናንትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመርተው አሸንፈዋል።’ ብለን እሱን እሱን አንስተን አውርተን ነበር። እና ወዲያው ነው የታነሳሳነው። ከዚያ በኋላ በእንቅስቃሴ የተሻልን ስለነበርን እንደውም ብዙ ኳሶች ሳትን እንጂ ከዚህም በላይ ማስቆጠር እንችል ነበር። ቡድኑ ጭንቀት ውስጥ የቆየ ቡድን አይመስልም ነበር። ያጣነው የፊት መስመራችንም ከሞላ ጎደል ዛሬ የተሻለ ነው ብዬ ነው የማስበው። ሲዲቤ ዛሬ ከቡድኑ ጋር መሆኑ የፊት መስመሩን ጠንካራ አድርጎታል ብዬ ነው የማስበው። የተሻልን ነበርን ዛሬ ውጤቱ ይገባናል።

ስለ ደስታ አገላለፁ

ቡድናችን የነበረበት ቦታ አይገልፀውም። ያው ብዙ ደጋፊ አለን ፤ ከእኛ ብዙ ነገር ይጠብቃል። በዛ ላይ ደግሞ ስቸገርበት የነበረው ነገር ሙሉ ለሙሉም ባይሆን በመጠኑ ስለተቀነሰ ለዛ ነው ደስተኛ የሆንኩት።

ስለ ሲዲቤ ቅጣት ምት

ያው መቺም ስለነበር ነው ፤ በልምምድ ላይም እየሰራ ስለነበር። ዳዊት እና እሱ ናቸው ቅጣት ምት የሚመቱት ፤ ግን እሱ የተሻለ ስለነበር ነው ዕድሉንም የሰጠነው በአግባቡ ተጠቅሞታል።

አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ

ቡድኑ መሪነቱን ማስቀጠል ስላለመቻሉ

አዎ በጣም አስቸጋሪ ነበር። እንደተጀማረ 20 ደቂቃ ምናምን ጥሩ ነበርን። ከዛ በኋላ ግን ቡድናችን ሁለት ቦታ መከፈል ጀመረ። የፈራሁት ነገር ነበር ፤ ሜዳው ለመጫወት ከባድ ነው። ነግሬያቸው ነበር ተጠንቅቀው ጉልበት ቆጥበው እንዲጫወቱ። መጨረሻ ላይ ራሳቸውን አዳክመዋል። ጥሩ አልነበርንም።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታ የሚመልስ ለውጥ ስላለመደረጉ

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ተጨዋች ቀይሪያለሁ። እየተመራህ ከሆነ አጥቅተህ ወይ አቻ ለመሆን ወይ ለማሸነፍ ስለሆነ የምትጫወተው በማጥቃት ለመጫወት ነው ሱራፌልን መሀል አድርጌ ኢታሙናን የቀየርኩት። ያው ኢታሙና እና ናንጄቤ በወረቀት ምክንያት አዲስ አበባ ነበሩ ፤ ከትናንት ወዲያ ነው የተቀላቀሉኝ። ልምምድም አልሰሩም ፤ ያው ሲገቡም የተሻለ ነገር አላሳዩም። ያው ካልሰራህ ጥሩ ነገር አትሰራም። ያው ጥሩ ነገር ይሰራሉ ብዬ ነበር ያስገባሁዋቸው። ጥሩ አልነበርንም ፤ ተሸንፈናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ