ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ7ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ምርጥ አቋማቸውን ያሳዩ ተጫዋቾችን እንዲህ መርጠናል።

አሰላለፍ 4-4-2

ግብ ጠባቂ

ዳንኤል ተሾመ – አዳማ ከተማ

እነ ሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ፍሬው ጌታሁን እና ጀማል ጣሰው ጥሩ ብቃት ባሳዩበት በዚህ የጨዋታ ሳምንት ምንም እንኳን አንድ ግብ ቢያስተናግድም ዳንኤል ተሾመ ልዩ ሆኖ ውሏል። አዳማ እንደ ዳንኤል ጥረት ባይሆን ኖሮ እጅግ በሰፊ የጎል ልዩነት ለመሸነፍ በተገደደ ነበር። ዳንኤል አምስት ኢላማቸውን የጠበቁ ከባባድ የወልቂጤ ሙከራዎችን በአስደናቂ ብቃት በማዳን ጥሩ ብቃት አሳይቷል።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ምንም እንኳን የጅማ የመጀመሪያ ጎል ለመቆጠሩ የእሱም አስተዋፅዖ የነበረበት ቢሆንም በቀሩት ደቂቃዎች ቡድኑ ባለድል እንዲሆን የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። ጨዋታው ሲጀምር በመስመር ተከላካይነት ቡድኑ ለውጦች ሲያደርግም በመስመር ተመላላሽነት ያገለገለው ሄኖክ ከፍ ባለ የማጥቃት ተሳትፎ የጌታነህን ሦስተኛ ግብ አመቻችቶ ሲያቀብል ራሱም ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።

ያሬድ ባየህ – ፋሲል ከነማ

የአፄዎቹ አምበል የሆነው ያሬድ ተጠባቂ በነበረው የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ በድኑ ተነሳሽነቱ ጨምሮ እንዲንቀሳቀስ አመርር በመስጠት ኃላፊነቱን የተወጣ ሲሆን ረጃጅም ኳሶችን በመቆጣጠር እና እንደሁል ጊዜውም በተረጋጋ አኳኋን ቅብብሎችን ከኋላ በማስጀመር ፋሲል ያለ ስጋት በማጥቃቱ ላይ እንዲያተኩር የበኩሉን አድርጓል።

ፈቱዲን ጀማል – ሲዳማ ቡና

በተከታታይ ጨዋታዎች ከሦስት የተለያዩ ተጫዋቾች ጋር በመሀል ተከላካይነት የተጣመረው ፈቱዲን ጥሩ ውሎ ያልነበረው ሰንደይ ሙቱኩን ክፍተት በመሸፈን እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች አጥቂዎችን በመቆጣጠር መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል። ሲዳማ ከመመራት ተነስቶ ባሸነፈበት በዚህ ጨዋታ ፈቱዲን እንደአምበልነቱ ቡድኑን የማነሳሳት ኃላፊነቱንም በሚገባ መወጣት ችሏል።

ደስታ ዮሐንስ – ሀዋሳ ከተማ

እንደ ቡድኑ ሁሉ በቅርብ ሳምንታት ወደ ቀደመ አቋሙ የተመለሰው በድጋሚ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቷል። በግራ መስመር ተመላላሽነት ጨዋታውን ጀምሮ በአሰልጣኝ ሙሉጌታ የታክቲክ ለውጥ ወደ መስመር ተከላካይነት ሚና የተለወጠውው ደስታ መስፍን ታፈሰ ያስቆጠራትን ወሳኝ ግብ አመቻችቶ ሲያቀብል በሁለቱም ሚናዎች በልበ ሙሉነት ማጥቃቱን ሲያግዝ እና ሲከላከል ተስተውሏል።

አማካዮች

ብርሀኑ አሻሞ – ሲዳማ ቡና

ከአራተኛው ሳምንት በኋላ ወደ አሰላለፍ ብቅ ያለው ብርሀኑ ለሁለተኛ ጊዜ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት ችሏል። በድሬዳዋው ጨዋታ ከፊቱ ከሚገኘው ዳዊት ተፈራ ጋር ጥሩ ቅንጅት የነበረው ብርሀኑ ጥቃቶችን በማቋረጥ እና የቡድኑን መልሶ ማጥቃቶች በማስጀመር ሲዳማ የሚታወቅበት ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከረጅም ጊዜ በኋላ እንዲያሳይ የበኩሉን አብርክቶት አድርጓል።

ዳዊት ተፈራ – ሲዳማ ቡና

የሲዳማን አብዛኛውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመራ የነበረው ዳዊት በታታሪነት ሰፊ ቦታ በመሸፈን የቡድኑ የልብ ምት መሆኑን ቀጥሎበታል። ወደ መስመሮች በመውጣት ጭምር ለሲዳማ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ሲያደርግ የነበረው አማካዩ ከአጥቂው ማማዱ ሲዲቤ ጋር የነበረው መናበብ ፍሬ አፍርቶም ለሲዳማ ሦስተኛ ግብ መቆጠር ምክንያት መሆን ችሏል።

ጋዲሳ መብራቴ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በመስመር አጥቂነት ጀምሮ የአሰልጣኝ ማሂርን ለውጥ ተከትሎ ደግሞ በመስመር ተመላላሽነት ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። ሁለቱን ሚናዎች ባማከለ መልኩ በመስመር አማካይነት የተጠቀምነው ጋዲሳ ቡድኑ አቻ እንዲሆን ላስቻለው ፍፁም ቅጣት ምት መገኘት መንስዔ የነበረ ሲሆን ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ በማድረግ የጊዮርጊስን የማጥቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን አድርጓል።

አብዱልከሪም ወርቁ – ወልቂጤ ከተማ

የቡድኑን የቀኝ ወገን የማጥቃት ሂደት ሲመራ የነበረው አብዱልከሪም ለተጋጣሚ የግብ ክልል ቀርቦ በታታሪነት ሲንቀሳቀስ ታይቷል። የመጀመሪያው የሆነውን የዋልያዎቹን ጥሪ በቅርቡ የተቀበለው አማካዩ በጨዋታው አንድ ግብ ለማስቆጠር ሁለተኛ ደግሞ ግብ የሆነ ኳስ ለማመቻቸት እጅግ ተቃርቦ የዳንኤል ተሾመ ምርጥ ብቃት ላይ መገኘት ብቻ ነበር ያገደው።

አጥቂዎች

ጌታነህ ከበደ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጌታነህ አሁንም ድንቅ አጥቂ እንደሆነ ያረጋገጠበትን ጨዋታ አከናውኗል። በሦስት የተለያዩ መንገዶች ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ የአንበሳውን ድርሻ የተወጣው ጌታነህ እንደአምበልነቱ የቡድን ጓደኞቹን በማነሳሳት በሙሉ ልብ ተጫውተው ውጤቱን እንዲቀለብሱ በማድረጉም በኩል ቁልፍ ሚና ነበረው።

ማማዱ ሲዲቤ – ሲዳማ ቡና

ማማዱ ሲዲቤ ከመጀመሪያው ሳምንት በኋላ ወደ አሰላለፍ ሲመለስ ሲዳማ ፊት መስመር ላይ ያጣውን ነገር ሁሉ ይዞ ተመልሷል። በጨዋታው ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አጥቂው የመጀመሪያውን ግብም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ሲዲቤ በእንቅስቃሴው ተዳክሞ ለሰነበተው ሀብታሙ ገዛኸኝ የሳጥን ውስጥ ነፃነትም ጉልህ ሚና ነበረው። በአጭሩ የሳምንቱ መረጥ ሊያስብለው የሚችለውን በቃት ማሳየት ችሏል፡፡

አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቡድናቸው ከመመራት ተነስቶ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል እንዲያስመዘግብ የአሰልጣኙ ሚና ከፍ ያለ ነበር፡፡ በተለይም በመከላከሉ ላይ አመዝኖ የነበረው ተጋጣሚያቸውን ለማስከፈት የተጨዋቾች አደራደር ለውጥ ያደረጉበት መንገድ እና ተጨዋቾች ውጤት ቀያሪ ሚና ኖሯቸው ጨዋታው ላይ በጎ ተፅዕኖ እንዲያሳርፉ ያደረጉበት መንገድ በማያሻማ መልኩ የሳምንቱ መረጥ አሰኝቷቸዋል፡፡

ተጠባባቂዎች

ሜንሳህ ሶሆሆ – ሀዋሳ ከተማ
ቶማስ ስምረቱ – ወልቂጤ ከተማ
እንየው ካሣሁን – ፋሲል ከነማ
ወንድምአገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ
ያስር ሙገርዋ – ሲዳማ ቡና
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ሲዳማ ቡና
ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ


© ሶከር ኢትዮጵያ