“የብሔራዊ ቡድን ምርጫ የመጀመርያዬም በመሆኑ ደስ ብሎኛል” ኤልያስ አታሮ

ከወራት በኃላ ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመጀመርያ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ካደረጉለት ኤልያስ አታሮ ጋር ጥሪው የፈጠረበትን ስሜት አስመልክቶ ከድረገፃችን ጋር ቆይታ አድርጓል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሀያ ስምንት ተጫዋቾችን ጥሪ ሲያደርጉ የጅማ አባ ጅፋሩ የመሐል እና ግራ መስመር ተጫዋች ኤልያስ አታሮን በእግርኳስ ተጫዋችነት ታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለታል። በቀደሞ መጠርያ ጅማ ከተማ አንስቶ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ ከነበሩ ቁልፍ ተጫዋች ከመሆኑ ባሻገር ጅማ አባ ጅፋር በ2010 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሲያነሳ የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበረ ይታወቃል። ምንም እንኳ ቡድኑ አባ ጅፋር ከሜዳ ውጭ ባሉ ባልተፈቱ ችግሮች ምክንያት በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ቢያደርግበትም ኤልያስ አታሮ በግሉ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ይገኛል። ለዚህም ይመስላል በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመጀመርያው የ28 ተጫዋቾች ስብስብ አካል ሆኗል። ይህን ጥሪ አስመልክቶ ኤልያስ አታሮ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከእኛ ጋር ቆይታ አድርጓል።

” ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ስሰማ እንደማንኛውም ሰው በጣም ተደስቻለሁ። የብሔራዊ ቡድን ምርጫ የመጀመርያዬም በመሆኑ ደስ ብሎኛል። ለመጠራትም ያበቃኝ ምክንያት ብዬ የማስበው ለአሰልጣኙ አጨዋወት በሆነ ነገር ይቀርባል ብሎ ስላሰበ ይመስለኛል። በግሌ ምክንያቱ ይሄ ነው ብዬ የማስበው። አሰልጣኙ ደግሞ የራሱ የተለየ ምክንያት አስቦ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ ትልቁ ነገር ቡድናችን ውስጥ ያሉ ችግሮች ቢኖሩም እኔ በግሌ የምሰራቸው ነገሮች እና ከቡድን ጓደኞቼ ጋር በሜዳ ውስጥ የማደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ጥሩ ነው ብሎ ስላመነ ይመስለኛል ለመመረጥ ያበቃኝ። መጠራቴ በራሱ ለቀጣይ እግርኳስ ህይወቴ ትልቅ ግብአት ነው። በዚህ ምርጫ ብቻ ይቆማል ብዬ አላስብም ከፈጣሪ ጋር ይቀጥላል ብዬ አስባለው። እኔም ጠንክሬ በሚቻለኝ ነገር ሁሉ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ለመቆየት እሰራለሁ።

” ኢትዮጵያ ውስጥ የግራ መስመር ተከላካይ እጥረት አለ ለሚባለው እግርኳስ ሒደት ነው። በአንድ ወቅት ጎልተው የሚታዩ አሉ። የሆነ ወቅት የሚጠፉ ይኖራሉ። እግርኳስ ሒደት ነው ከዛ አንፃር ይሆናል እንጂ በየቡድኑ የተሻሉ አቅም ያላቸው ልጆች አሉ።

“አባ ጅፋር ዝግጅት የጀመርንበት ጊዜ አጭር መሆኑ እና ምንም የወዳጅነት ጨዋታ ሳናደርግ ወደ ውድድር መግባታችን ክፍተት ፈጥሮብናል። ይሄም ቢሆን እስካሁን ባለው የቡናችን ጉዞ ውስጥ አሸንፈን ሦስት ነጥብ አናግኝ እንጂ አሸንፈን መውጣት የምንችላቸው ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ የጣልንበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነው። አሁን ወደ ትክክለኛ እንቅስቃሴ እየገባን ቡድናችን እየተሟላ ነው። በቀጣይ የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ