“አስመስሎ የምወድቅ ተጫዋች አይደለሁም፤ ዋናው መታየት ያለበት ነገር …”

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ ዓመት ውድድር ወጥ የሆነ አቋም በማሳየት ላይ የሚገኘው አቡበከር ናስር ይሄን ይናገራል።

እስካሁን ባለው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የተሳካ ጉዞ ያደረገ ይገኛል። በሸገር ደርቢ የመጀመሪያ ግቡን ከማስቆጠር አልፎ ሐት-ትሪክ የሰራው አቡበከር በኢትዮጵያ ቡና የውጤት ጉዞ ውስጥ በየጨዋታው ሁሉም ነገር እያደረገ ይገኛል። በስምንት ጎል የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን ከሙጂብ ቃሲም ጋር በመስተካከል እየተፎካከረ የሚገኘው አቡበከር የፍፁም ቅጣት ምቶች መገኘት ምክንያት ከቡድን አጋሮቹ ጋር መሆኑ እና የተገኙትን አጋጣሚዎች ወደ ጎልነት የሚቀይር መሆኑን ተከትሎ “ሆን ብሎ በመውደቅ ዳኞችን በማሳሳት የፍፁም ቅጣት ምትን ያገኛል።” የሚል አስትያየቶች ሲሰጡ ይሰማል። ይህን መነሻ በማድረግ ለአቡበከር ጥያቄ አቅርበንለት ተከታዩን አጭር ምላሽ ሰጥቷል።

” አስመስሎ የሚወድቅ ተጫዋች አይደለሁም። ዋናው መታየት ያለበት ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳሱን ይዘን የምንገባበት ሒደት ነው። ብዙ ሰው ፍፁም ቅጣት ምት የሚረዳበት መንገድ ይለያል። እኔ ሆን ብዬ ዳኛን ለማሳሳት የምወድቅበት መንገድ የለም። በትክክል ኳሱን ይዤ ተከላካይ ለማለፍ ስገባ በሚሰራብኝ ጥፋት ነው የምወድቀው እንጂ አወዳደቄን አሳምሬ አልወድቅም። ወደ ፊትም መታየት ያለበት ነገር ቡድናችን ኳስን ተቆጣጥሮ ጎል ለማስቆጠር በሚያደርገው ሂደት ውስጥ በተደጋጋሚ በሚሰሩብን ጥፋቶች ትክክለኛ ፍፁም ቅጣት ምት እንደምናገኝ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ