የወልዲያ ስታድየም ውድድር ሊካሄድበት የሚችልበት ዕድል እንዳለ ተሰምቷል

በኢትዮጵያ ስታድየም ግንባታ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን የተደረገው በወልዲያ ከተማ የተገነባው የሼክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም በቅርቡ ውድድር ሊያዘጋጅ እንደሚችል እየተሰማ ይገኛል።

መቻሬ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በክቡር የሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ወጪ 25 ሺህ ተመልካች እንዲይዝ ተደርጎ ከአራት ዓመታት ግንባታ በኃላ በጥር ወር በ2009 ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃቱ ይታወቃል። ወልዲያ በፕሪምየር ሊጉ እና በከፍተኛ ሊግ ዓምና በኮቪድ ምክንያት እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ውድድሮችን ሲያካሂድ የሰነበተው ስታድየሙ የ2013 የከፍተኛ ሊግ ውድድሮችን እንዲያስተናግድ ከተመረጡ ሜዳዎች መካከል አንዱ በመሆን ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ በወቅታዊ ሀገራዊ ችግር ምክንያት ውድድሩን ወደ ሌላ ሜዳ መቀየሩን ተከትሎ በአሁን ሰዓት የሼክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም ምንም አይነት አገልግሎት እየሰጠ አይገኝም።

በዚህ ምክንያት የከተማው አስተዳደር እና ህዝቡ ስታዲየሙ የከፍተኛ ሊግ ውድድር እንደሚካሄድበት ከተመረጠ በኃላ ለውጥ መደረጉ ቅሬታ ሲፈጥር መቆየቱን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት በቀጣይ ጊዜያት የከፍተኛ ሊግ ውድድርን ወልዲያ ላይ ዳግመኛ ለማድረግ እቅድ እንዳለው እና የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ ኮሚቴም ከጊዜ በኋላ በይፋ እንደሚያሳውቅ ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ