ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዲቪዚዮን | ባህር ዳር ከተማ እና ጥሩነሽ አካዳሚ ተጋጣሚያቸውን አሸንፈዋል

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በሁለት ጨዋታ ሲጀምር ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ እና ባህር ዳር ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

ከውጤት ቀውስ ጋር ተያይዞ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዮናስ ወርቁን ያገደው ልደታ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ነው በጥሩነሽ ዲባባ በሰፊ የጎል ልዮነት ለመሸነፍ የተገደደው። ጥሩነሽ አካዳሚዎች በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ ጎል ለማስቆጠር የነበራቸው ፍላጎት ስኬታማ መሆን የጀመረው ገና በአራተኛው ደቂቃ ነው። ሂሩት ተስፋዬ ከመዐዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሯ ገጭታ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ መሆን የቻሉት። ብዙም ሳይቆይ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል አንስተው ኳሱ ሳይቋረጥ አደራጅተው በመሄድ በ6ኛው ደቂቃ በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የተመለከትናት ጤናዬ ለታሞ በጥሩ አጨራረስ ጎል በማስቆጠር የጥሩነሽ ዲባባን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች።

በደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ጎል በማስተናገዳቸው አለመረጋጋት ውስጥ የገቡት ልደታዎች ተጨማሪ ጎሎች ሊያስተናግዱ የሚችሉበትን ስህተት በተደጋጋሚ ቢሰሩም ጥሩነሽ አካዳሚዎች ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። የጨዋታውን እንቅስቃሴን በኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ የቻሉት አካዳሚዎች በ36ኛው ደቂቃ በእመቤት ፋንታሁን እና በ43ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ጤናዬ ለተሞ ሦስተኛ እና አራተኛ ጎል አስቆጥረው ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ልደታዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በመከላከሉ የነበራቸውን ክፍተት በማረም ጎል እንዳይቆጠርባቸው በማድረግ በኩል ተስተካክለው ቢመጡም በማጥቃቱ በኩል የነበራቸው እንቅስቃሴ ስኬታማ ባለመሆኑ ይህን ያህል የጎል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንፃሩም በመጀመርያው አጋማሽ አራት ጎል ማስቆጠራቸው ጨዋታውን የጨረሱ መስሏቸው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የተቀዛቀዘ ቢሆንም መሐል ሜዳ ላይ ከወሰዱት ብልጫ ውጭ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያ 90ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ኢማን ሽፋ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ ወደ ጎልነት በመቀየር የጥሩነሽ ዲባባን ጎል ወደ አምስት ከፍ ያደረገ የማሳረጊያ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በጥሩነሽ ዲባባ 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አስር ሰዓት በቀጠለው የዛሬው ሁለተኛ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል ወሳኝ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችሏል። ጨዋታው እምብዛም የጎል ምከራ ያልተደረገበት እና ጥንቃቄ የበዛበት ጨዋታ ቢሆንም በሁለቱም በኩል አልፎ አልፎ ለጎል ያልቀረበ ቢሆንም ሙከራዎች ይደረጉ ነበር። በተለይ በሻሸመኔ በኩል ዓለሚቱ ድሪባ ከግብጠባቂዋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ያመከነችው እንዲሁም በባህር ዳር በኩል ትዕግስት ወርቁ ያልተጠቀመችበት የጎል አጋጣሚ ተጠቃሽ የሚሆን ነው። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ያለ ጎል ይጠናቀቃል ሲባል ለባህር ዳር ተቀይራ በመግባት ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት የቻለችው ሠብለወንጌል ወዳጆ 80ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 1–0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ የሊጉ መሪ መሆን ችሏል።

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የነገ የረቡዕ ጥር 5 ቀን ጨዋታ

04:00 | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ለገጣፎ
10:00 | ቂርቆስ ከ ቦሌ


© ሶከር ኢትዮጵያ