ወላይታ ድቻን ለማሰልጠን ከሃያ ሦስት በላይ አሰልጣኞች የሥራ ማስረጃቸውን አስገብተዋል

ከውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ አሰልጣኙን አሰናብቶ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር በወጣው ማስታወቂያ ከሃያ ሦስት በላይ አሰልጣኞች የሥራ ማስረጃቸውን አስገቡ።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ዋና አሰልጣኙ ደደለኝ ደቻሳ እና ምክትሉ ግዛቸው ጌታቸውን ያሰናበተው ወላይታ ድቻ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ከሀያ ሦስት በላይ አሰልጣኞች የሥራ ልምዳቸውን እና የትምህርት ማስረጃቸውን እስከ ትናንት ማምሻ ድረስ ማስገባታቸውን ሰምተናል። በወጣው መስፈርት መሠረት ካስገቡት በርከት ያሉ አሰልጣኞች መካከል ዘላለም ሽፈራው፣ ፀጋዬ ኪዳነማርያም፣ አዲሴ ካሣ፣ ሲሳይ አብርሀ፣ ሰብስቤ ይባስ፣ እዮብ ማለ፣ ግርማ ሀብተዮሐንስ በሊጉ ልምድ ካላቸው የሚጠቀሱ ናቸው።

በትናንትናው ዕለት ተጠቃሎ የገባውን ማስረጃ የክለቡ ቦርድ ከመረመሩ በኋላ ቡድኑ በቀጣይ ዓርብ ጅማ ላይ ከሚጠብቀው የሰበታ ከተማ ጨዋታ በፊት ምንአልባትም ዛሬ ማታ የዋና አሰልጣኙን በመሾም ይፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ