የአዲስ አበባ ስታዲየም የዕድሳት ሥራ ለማከናወን የዲዛይን፣ የማማከር እና የቁጥጥር አገልግሎት ከሚሠራ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት መደረጉን የስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል ።
የዲዛይን፣ የማማከርና የቁጥጥር አገልግሎቱን የሚያከናውነው ዮሐንስ ዓባይ አማካሪ አርክቴክቸር እና ኢንጅነሪንግ በተባለ ድርጅት ሲሆን የዲዛይን ስራውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ የሚያቀርብ ይሆናል። የዲዛይን ሥራው የካፍ ስታንዳርድን ጠብቆ እንደሚሰራ ለማወቅ ተችሏል።
72 ዓመታት ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በዕድሜ ብዛት ዘመኑን የሚመጥን ስላለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ሲሆን ካፍ ዓለምአቀፍ ውድድሮች እንዳይደረጉበት ማገዱ ይታወሳል። ዘንድሮ 36 የሊግ እና አራት ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ያደረገው ስታዲየሙ መጠነ ሰፊ እድሳት ከተደረገለት ረጅም ዓመታት አልፈውታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ