ወላይታ ድቻ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

በቅርቡ ዋና አሰልጣኙ እና ምክትሉን ያሰናበተው ወላይታ ድቻ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት የክለቡ የቦርድ አመራር አወዳድሮ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ታውቋል።

ትናንት ረፋድ ላይ በነበረው ዘገባችን ከ23 በላይ አሰልጣኞች ወላይታ ድቻን ለማሰልጠን የትምህርት ማስረጃቸውን ማስገባታቸውን እና የክለቡ ቦርድ ኃላፊዎች ቡድኑ በቀጣይ ዓርብ በሰባተኛ ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጨዋታ አስቀድሞ የዋና አሰልጣኙን በመሾም ይፋ የሚያደርግ መሆኑን መግለፃችን ይታወቃል። በዚህ መሠረት የክለቡ አመራር አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩን ለማረጋገጥ ችለናል።

አሰልጣኝ ዘላለም ከሚኖሩበት ሀዋሳ ከተማ ወደ ወላይታ ሶዶ በማቅናት በአንዳንድ ሁኔታዎች ስምምነት ካደረጉ በኃላ ቡድኑ ካጋጠመው ወቅታዊ የውጤት ከቀውስ በማውጣት ውጤታማ እንደሚያደርጉት የክለቡ አመራሮች እምነት መጣላቸውን አሳውቀዋቸዋል። በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ አሰልጣኙ ረዳቶቻቸውን የሚያሳውቁ ሲሆን ክለቡንም ወደ ነበረበት ጥንካሬ የመመለስ ኃላፊነትን ተረክበዋል። አሰልጣኝ ዘላለም ቡድኑ ወደ ሚገኝበት ጅማ ከተማ ዛሬ በመጓዝ የመጀመርያ ሥራቸውን ነገ በ09:00 ሰበታ ከተማን በመግጠም የሚጀምሩ ይሆናል።

አሰልጣኝ ዘላለም ዓምና ከመከላከያ ጋር ከመለያየታቸው በፊት ከዚህ ቀደም በአዳማ ከተማ፣ ደደቢት፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልዲያ እና ደቡብ ደቡብ ፖሊስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ረዳት) ማሰልጠናቸው ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ