የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ አዘጋጅ ከተማ የሆነችው ጅማ ከረጅም ዓመት በኃላ የሀገሪቱን ትልቁን ውድድር ለማስተናገድ በምን ሁኔታ እንደምትገኝ የዳሰስንበት ወቅታዊ መረጃዎችን እናጋራችሁ።
የአፍሪካ ክለቦች ዋንጫን እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች በቀድሞ ዘመን ታዘጋጅ የነበረው ጅማ ከተማ ከረጅም ዓመት በኃላ የሀገሪቱን ትልቅ ውድድር የሆነውን የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከሰባተኛ ሳምንት እስከ አስራ አንደኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት ዕድሉን ማግኘቷ ይታወሳል። ሶከር ኢትዮጵያም እያንዳንዱን ኩነት ከስፍራው ለመዘገብ ወደ ከተማዋ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ ጅማ ውድድሩን ለማድረግ የሚያስችሉ አብዛኛውን ቅድመ ሁኔታዎች በሟሟላት የውድድሩን መጀመር እየጠበቀች መሆኑን በከተማዋ ቅኝት ባደረግንበት ወቅት የታዘብነውን ምልከታ እንዲህ ቃኝተነዋል።
* ሰበታ ከተማ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ለውድድሩ መጀመር ጥቂት ቀናት ሲቀረው ወደ ጅማ ከተማ ከመግባታቸው ውጭ አብዛኛው ክለቦች ቀደም ብለው በመግባት ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። የሰባተኛው ሳምንት አራፊ ቡድን የሆነው ኢትዮጵያ ቡና በቀጣዩ ሳምንት ሰኞ ጅማ እንደሚገባ ለማወቅ ችለናል።
* ጨዋታውን የሚያስተናግደው የጅማ ዩንቨርሲቲ ሜዳን ለጨዋታው ምቹ ለማድረግ በርከት ያሉ ስራዎች ሲሰሩ የተመለከትን ሲሆን ሜዳው እጅግ በጥሩ ሁኔታ መሰራቱን በአካል በሜዳው ተገኝተን ለመታዘብ ችለናል።
* ከጨዋታው በ48 ሰዓት በፊት ሁሉም ቡድኖች የኮቪድ ምርመራ የሚያደርጉበት ጣብያ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ እጅግ በተሟላ ሁኔታ የተዘጋጀ መሆኑ ለማየት ችለናል።
* ጨዋታውን በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፈው ሱፐር ስፖርት 29 የቡድን አባላት አስቀድመው ጅማ የገቡ ቢሆንም ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የማሰራጫው ተንቀሳቃሽ መኪና እስካሁን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጅማ አለመግባቱን ለማረጋገጥ የቻልን ሲሆን ምን አልባትም ቴክኒካል ስራው ላይ መዘግየታቸው በነገው የቀጥታ ስርጭት ላይ ተፅእኖ እንዳያደርግ ተሰግቷል።
* በሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሠይፉ የሚመራው የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ አብዛኛዎቹ አባላት ጅማ ከተማ የገቡ ሲሆን የሊግ ኮሚቴው የቦርድ አመራሮች ማምሻውን እንደሚገቡ ሠምተናል።
* የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውድድሩን የሚመሩ አስራ ሦስት ዋና ዳኞች እና አስራ ሦስት ረዳት ዳኞች በድምሩ 26 ዳኞች በመያዝ ከሁለት ቀን በፊት ጅማ የገቡ ሲሆን ከዳኞቹ መሐል አንድም ሴት ዳኛ እንደሌለ ለማወቅ ችለናል። በተመሳሳይ የጨዋታ ታዛቢ ኮሚሽነር አባላት ጅማ መግባቱን አረጋግጠናል።
* ጨዋታውን በቀጥታ ስርጭት በአማርኛ ቋንቋ ለማስተላለፍ ጋዜጠኛ መኳንት በርሔ፣ ማርቆስ ኤልያስ በተንታኝነት ኃይለእግዚአብሔር አድኀኖም ጅማ ከተማ የተገኙ ሲሆን ከዚህ ቀደም እንደነበረው ከቀድሞ ተጫዋቾች መካከል አዳነ ግርማ፣ ጌታቸው ካሳ እና ሳምሶን ሙልጌታ በተንታኝነት ያገለግሉ የነበረ ቢሆንም በጅማው ውድድር ምንም ዓይነት የቀድሞ ተጫዋቾች እንደማይኖሩ ለማወቅ ችለናል።
* የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አባላት ውበቱ አባተ እና አስራት አባተ አስቀድመው በመገኘት የተሳካ ባይሆንም መጠነኛ ዝግጅት ያደረጉ ሲሆን እዚሁ ጅማ በመቆየት የመረጧቸውን እና ሌሎችን ለመመልከት በየጨዋታዎቹ እንደሚገኙ አውቀናል።
* የኢትዮጵያ እግርኳስን ፌዴሬሽንን በመወከል የሥራ አስፈፃሚው አባል አቶ ኢብራሂም እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን የቴክኒክ ኮሚቴው ውድድሩን ለመገምገም አለመኖሩ አስገራሚ ሆኗል።
* ጨዋታው የሚካሄድበትን ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ውጫዊ ገፅታን ለማስዋብ የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች በዛሬው ዕለት የፅዳት ዘመቻ አድርገዋል።
* እንግዶቿን ለአንድ ወር ተቀብላ የምታስተናግደው ጅማ ከተማ በከንቲባው የበላይ ጠባቂነት ከፀጥታ አኳያ ያለምንም ስጋት ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንግዶቿን ተቀብላ ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኗን የከትማው የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ገልፀዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ