ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ሰበታ ከታማ

የሰባተኛ ሳምንቱን ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እነሆ።

አዲስ አበባ ላይ አራት ተከታታይ ሽንፈቶች የገጠሙት ወላይታ ድቻ ወደ ጅማ ከዞረው ውድድር የማገገም ግዴታ ውስጥ ሆኖ ሰበታን ይገጥማል። አዳማን ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ የአቻ ውጤት እንኳን ማሳካት ያልቻለው ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ እና ረዳታቸውን አሰናብቶ በአዲስ አመራር ውድድሩን የሚቀጥል ይሆናል። በዋና አሰልጣኝነት ቦታው ላይ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን የሾመው ድቻ ሜዳ ላይ በሚኖረው እንቅስቃሴ በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት የሚታዩ ጊዜያዊ የቡድን መነቃቃቶች ሊታዩበት ይችላሉ። ይህ ከሆነም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየቀነሰ የመጣውን የታታሪነት ደረጃውን ሊያሻሽለው ይችላል። በተለይም ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ላይ መበታተን የሚታይበት ድቻ በዚህ ስሜት ውስጥ ወደ ሜዳ የሚገባ ከሆነ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ማግኘት ላይ የሚያተኩረው ተጋጣሚው ክፍተቶች እንዳያገኝ በማድረጉ ረገድ ለውጥ ሊታይበት ይችላል። ከጨዋታው ውጤት ለማግኘት ግን በስድስቱም ጨዋታዎች ቢያንስ አንድ ግብ ሳያስቆጥር የማይወጣው ድቻ በተመሳሳይ ግቦችን ማግኘት የግድ ይለዋል።

እንደ ድቻ ሁሉ ከአንድ ድል ውጪ ማስመዝገብ ያልቻለው ሰበታ የተጋጣሚውን ያህል የውጤት ቀውስ ውስጥ ባይገኝም በቶሎ ወደ አሸናፊነት መመለስ ግን ይጠበቅበታል። ይህን ለማድረግ የሚረዱ ግቦችን ለማግኘት ቡድኑ የሚመርጠው የኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አቀራረብ በነገውም ጨዋታ እንደሚቀጥል ይታሰባል። እንደጅማው ጨዋታ ሁሉ ተጋጣሚው ቀድሞ ግብ ካገኘ ግን ክፍተቶችን ለመማግኘት ቀላል የሚሆንለት አይመስልም። ለዚህም ቅብብሎችን ፈጠን በማድረግ በቶሎ ግብ ላይ ለመድረስ እና የፊት አጥቂዎቸን ፍጥነት ለመጠቀም የሚሞክር ዓይነት አጨዋወት ከሰበታ አማካዮች የሚጠበቅ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ያለግብ ከተጠናቀቀው የድሬው የሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ውጪ በሁሉም ጨዋታዎች ግብ እያስተናገደ የሚገኘው ቡድኑ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ እየወረደ የሚመጣው የመከላከል አደረጃጀቱን አስተካክሎ መቅረብ ይጠቀምበታል።

ወላይታ ድቻን ለማሰልጠን ኃላፊነት የተረከቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የነገውን ጨዋታ የሚታደሙ ሲሆን ቡድኑን የሚመራው ግን የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ ዘላለም ማቲዮስ ይሆናል። በጨዋታው ድቻ ጉዳት ላይ የሚገኙት ስንታየሁ መንግሥቱ እና እዮብ ዓለማይሁን ግልጋሎት እንደማያገኝ የሰማን ሲሆን የሰበታ ከተማን የቡድን ዜና ለማካተት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት
ሰበታ ከተማ 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ የመጀመርያ ግንኙነታቸው ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-2-3-1)

ሰዒድ ሀብታሙ

አናጋው ባደግ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ – አማኑኤል ተሾመ

ፀጋዬ ብርሀኑ – እንድሪስ ሰዒድ – ቸርነት ጉግሳ

ያሬድ ዳርዛ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጻውሎስ – አዲስ ተስፋዬ – ያሬድ ሀሰን

ቢያድግልኝ ኤልያስ – መስዑድ መሀመድ

ፉዓድ ፈረጃ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ታደለ መንገሻ

ፍፁም ገብረማርያም


© ሶከር ኢትዮጵያ