ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በጅማ የሚጀምርበትን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

የአዲስ አበባ ቆይታውን ያለምንም ድል ያጠናቀቀው ጅማ አባ ጅፋር በመቀመጫ ከተማው በሚደረገው ቀዳሚው ጨዋታ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ ለማሳካት ያልማል። ከሀዋሳ እና ሰበታ ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ መጋራት የቻለው ጅማ የጨዋታ አቀራረቡም ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጥ ሆኖ ታይቷል። ይህ ሂደት እስካሁን አሸናፊ ባያደርገውም ከሽንፈት መራቅ ስላስቻለው ነገም በተመሳሳይ ሁኔታ ጊዮርጊስን እንደሚገጥም መገመት ይቻላል። ያም ቢሆን የቡድኑ ጥብቅ መከላከል ግብ ሳያስተናግድ ለመውጣት ያላገዘው በመሆኑ ይበልጥ ክፍተቶቹን አስተካክሎ መቅረብ ይኖርበታን።

አባ ጅፋር አንድ ነጥብ አግኝቶ በወጣባቸው ሁለቱም ጨዋታዎች ከቆሙ ኳሶች መነሻነት ግቦች የተቆጠሩበት መሆኑ እና በወቅቱ አግቢዎቹ በጅማ ሳጥን ውስጥ የነበራቸው ነፃነት ሲታይ መሰል ስህተቶች ነገም ዋጋ እንዳያስከፍሉት ያሰጋዋል። በማጥቃቱም ረገድ ቡድኑ በራሱ ሜዳ ላይ ረጅም ደቂቃዎችን ከማሳለፉ አንፃር የተጠና የመልሶ ማጥቃት ሂደትን ሲተገብር አለመታየቱ ግብ የማግኛ መንገዶቹን ውስን አድርገውበታል። ይህም ከጊዮርጊስ ተከላካዮች ጀርባ የሚኖረውን ክፍተት የመጠቀም አቅሙን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ጉዳይ ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሦስት ተከታታይ ድል ጉዞው በሸገር ደርቢ ሽንፈት ከተገታ በኋላ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የነገውን ጨዋታ ይጠብቃል። በቡናው ጨዋታ ከ75 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ፈረሰኞቹ በጨዋታው ላይ እንደቡድን ውጤት ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነበር። ያም ቢሆን የግራ ወገኑ የቡድናቸው የመከላከል ክፍል በቀላሉ ለተጋጣሚ ተጋልጦ መታየቱ ለእንደነገው ዓይነት ጨዋታዎች ስጋትን የሚጭር ነው። ይህ የቡድኑ ድክመት ካልታረመ በረሱ ሜዳ ላይ ብዙውን ጊዜ ሊያሳልፍ ለሚችለው ጅማ መልሶ ማጥቃት በር ሊከፍት ይችላል።

የኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ አቀራረባቸውን ሙሉ ለሙሉ ባይቀይሩም ቀጥተኝነት እየተንፀባተቀባቸው ያሉት ጊዮርጊሶች ከጅማ ጋር በሚኖረው ጨዋታ ክፍተት የማይሰጥ ተጋጣሚን ሰብሮ የመግባት ጥንካሪያቸው መፈተሹ የሚቀር አይመስልም። በዚህም የሜዳውን ስፋት አብዝቶ ለመጠቀም የሚሞክር እና በፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የኋልዮሽ እንቅስቃሴ ጭምር በርከት ያሉ ቅብብሎችን በተጋጣሚው ሜዳ ላይ የሚከውን ዓይነት ቡድን ከፈረሰኞቹ ይጠበቃል። በመጀመሪያው እና በመጨረሻው የአዲስ አበባ ጨዋታዎቹ የግብ ጠባቂዎች ስህተት ዋጋ ያስከፈለው ቡድኑ ይህ ድክመቱ ሌላው በጨዋታው ለኪሳራ ሊዳርገው የሚችል ነጥብ ነው።

ጅማ አባ ጅፋር ጉዳት ላይ የሰነበተው መሀል ተከላካዩ ከድር ኸይረዲን ቢመለስለትም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ከመሆኑ በቀር ቀሪ ስብስቡ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኖለታል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ደስታ ደሙ ብቻ ጉዳት ላይ የሚገኝ ሲሆን አቤል ያለውን ጨምሮ ሌሎች የረጅም ጊዜ ጉዳት የነበረባቸው ተጫዋቾችም ማገገማቸውን ሰምተናል። የአቤል የነገ ጨዋታ ቀዳሚ ተሰላፊነት ግን እርግጥ አልሆነም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ጊዜ ድል ሲያስመዘግብ ጅማ አባ ጅፋር አንድ ጊዜ አሸንፏል። ቀሪውን ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

– በአራቱ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ 6 ጎሎችን ሲያስቆጥር፤ ጅማ 2 ጎሎችን አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ወንድምአገኝ ማርቆስ – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ – ተመስገን ደረሰ

ሱራፌል ዐወል – ንጋቱ ገብረስላሴ– ሙሉቀን ታሪኩ

ሮባ ወርቁ – ሳምሶን ቆልቻ – ሳዲቅ ሴቾ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

ሀይደር ሸረፋ – ሙሉዓለም መስፍን

ጋዲሳ መብራቴ – ሮቢን ንግላንዴ – አዲስ ግደይ

ጌታነህ ከበደ


© ሶከር ኢትዮጵያ