የከፍተኛ ሊግ | የከፍተኛ ሊግ የዛሬ ውሎ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዚህ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በተካሄዱ የምድብ ሀ እና ለ ጨዋታዎች ተገባዷል።

ምድብ ሀ

በባቱ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የምድብ ተ በአራተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎው የምድቡ ጠንካራ ቡድኖች የሆኑት መከላከያ እና ደሴ ከተማን አገናኝቶ በደሴ 2-0 ተጠናቋል። ተከታታይ ድል ያስመዘገቡ ቡድኖችን ያገናኘ ከመሆኑ አንፃር ትልቅ ግምት አግኝቶ በነበረው ጨዋታ ደሴዎች የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ በረከት አድማሱ በሃያኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ግብ አቆጥሮ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩ ሲሆን ከእረፍት መልስ በሦስቱም ጨዋታዎች ጥሩ አጥቂነቱን እያሳየ የሚገኛው የቀድሞ የደደቢት ተጫዋች አኩየር ቻም የደሴ ከተማ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል ።

በ9:00 ላይ ወልድያን ከ ገላን ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በገላን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በአሰልጣኝ በፀሎት እየሰለጠነ የሚገኘው ገላን ከተማ ጥሩ በመልካመም አጀማምሩ እንዲቀጥል ያደረገችውን ወሳኝ ጎል አብዱልለጢፍ ሙራድ አስቆጥሯል።

ምድብ ለ

2:00 ሲል ጋሞ ጨንቻን ከ ሀላባ ከተማ በመጀመሪያ የዕለቱ ጨዋታ አገናኝቷል፡፡ ብዙም ሳቢ ባልነበረው እና በእንቅስቃሴ ሆነ በሙከራ ረገድ ደከም ባለው በዚህ ጨዋታ ላይ ጋሞ ጨንቻዎች በተወሰነ መልኩ የነበራቸው የማጥቃት ሀይል እጅጉን መልካም የሚባል ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሳካ የሜዳ ላይ ቆይታ የነበራቸው ጋሞ ጨንቻዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ አሸናፊ ተገኝ የሀላባን ፍጹም የመከላከል ድክመት ተጠቅሞ ጋሞ ጨንቻን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡አሁንም በተወሰነ ረገድ ተሽለው በአጋማሹ የታዩት ጋሞዎች 38ኛው ደቂቃ ላይ እንደ መጀመሪያው አጋማሸ ተመሳሳይ ከሆነ አቅጣጫ የተገኘን ኳስ አሸናፊ ተገኝ ለራሱም ሆነ ለጋሞ ጨንቻ ሁለተኛ ጎል ከመረብ አሳርፎ ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ሀላባ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ጋሞ ጨንቻቸው አስጠብቆ ለመውጣት በሜዳ ላይ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡ ስኬታማ የሆነ ግልፅ የሙከራ ሂደቶች በጨዋታው ባይታይም ሀላባ ከተማ በሜዳ ላይ ሲያሳይ የነበረው ተነሳሽነት አስገራሚ ሆኖም 65ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የሀድያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ የመስመር አጥቂ እዮኤል ሳሙኤል በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ጨዋታው በጋሞ ጨንቻ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

7:00 ሲል በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሁለቱ የደቡብ ምዕራብ ቡድኖች ካፋ ቡና እና ቤንች ማጂ ቡናን አገናኝቷል፡፡ እጅግ ፀሀያማ በነበረው እና የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሳር ለተጫዋቾቹ ሙቀታማ በመሆኑ በሜዳ ላይ ተቸግረው ባየንበት እና በተደጋጋሚ ጫማቸው ላይ ውሀን በመድፋት ጭምር ከባዱን ጨዋታ ባደረጉበት መርሀ ግብር ተመሳሳይ የጨዋታ ቅርፅን ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሜዳ ይዘው የገቡ ሲሆን ረጃጅም ተደራሽነት የሌላቸው ኳሶችን በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ የታየበት ሙሉ የጨዋታው ደቂቃ ሁነቶች ናቸው፡፡ ሆኖም በመጀመሪያው አጋማሸ የቤንች ማጂው አምበል ወንድማገኝ ኪራ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ከመረብ ያሳረፋት ብቸኛ ጎል ቤንች ማጂ ቡናን አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል፡፡

የዕለቱ የመጨረሻ የምድቡ ጨዋታ ሀምበሪቾ ዱራሜን ከ ከጅማ አባቡና ያገናኘው ነበር፡፡ ፈጣን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታዎች የመጀመሪያው አርባ አምስት ከእንቅስቃሴ አንፃር ተመሳሳይ ይዘት የነበረው ቢሆን ከመስመር በሚነሱ የጠሩ ዕድሎች ተጋጣሚን በማሴጨነቅ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ተሽለው የቀረቡበት ነበር፡፡ በተለይ ፈጣኑን የመስመር አጥቂ ብሩክ ኤሌያስን ማዕከል ባደረገው የቀኝ መስመር የሽግግር እንቅስቃሴ ሀምበሪቾዎችን 21ኛው ደቂቃ አቦነህ ገነቱ የፈጠረለትን ተሻጋሪ ኳስ ተጠቅሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሐራዊ ቡድን ኮከብ ራምኬል ሎክ ለሀምበሪቾዎች ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡በተመሳሳይ ዳግም በቀለ ሁለተኛ ጎል ሊሆን የሚችል ዕድልን ከሁለት ደቂቃ በኃለዋልታ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ መልሶ ማጥቃትን ምርጫቸው ለማድረግ የተገደዱት ጅማ አባቡናዎች በተመስገን ድንቁ አማካኝነት እጅግ ለጎል ቢቀርቡም የግቡ ቋሚ ብረት አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን ዕድል አሳጥቷቸዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ማጥቃት ላይ የነበራቸውን ክፍተት ለመቅረፍ አከታትለው ተጫዋች የለወጡት ሀምበሪቾዎች ቅያሬያቸው የተሳካላቸው እንደነበር ተቀይረው የገቡት ተጫዋቾች ማሳያዎች ናቸው፡፡የጅማ አባቡናን የእንቅስቃሴም ሆነ ወደ ፊት ለማጥቃት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቆጣጠሩም የተዋጣላቸው እንደነበሩ በቀሪው ደቂቃ መመልከት የቻልንበትን ሂደት ማስተዋል ችለናል፡፡ በተለይ አጥቂው ቢኒያም ጌታቸው ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ተቀይሮ ከገባበት ደቂቃ አንስቶ ሲያሳይ የነበረበት እንቅስቃሴ ተጠቃሹ ነበር፡፡ በአንፃሩ ጥቂት የማይባል አጋጣሚን የሀምበሪቾን ተከላካይ መዘናጋት ለመጠቀም አባቡናዎች የታተሩ ቢሆንም የነበራቸው ደካማ የአጨራረስ ብቃት ኃላ ላይ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ጨዋታው በዚህ ሂደት ቀጥሎ 68ኛው ደቂቃ ላይ አምረላ ደልታታ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከአምስት ዓመት የደቡብ ፖሊስ ቆይታ በኋላ ሀምበሪቾን የተቀላቀለው ብሩክ ኤልያስ በግንባር ገጭቶ ሁለተኛ ጎል ለሀምበሪቾ አስቆጥሮ የክለቡን የግብ መጠን ከፍ አድርጓል፡፡ አሁንም ጎል ለማስቆጠር ሲጥሩ የታዩት ሀምበሪቾዎች በቢኒያም ጌታቸው አማካኝነት ግሩም ሦስተኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታው በቀሪ ደቂቃ ምንም ሳንመለከትበት በሀምበሪቾ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የከፍተኛ ሊጉ ቀጣይ መርሐ ግብር ከቀናት በኋላ እንደሚካሄድ ሲጠበቅ ፕሮግራሙ ከአወዳዳሪው አካል ሲደርሰን የምናቀርብ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ