ቅዱስ ጊዮርጊስ በጌታነህ ከበደ ሐት-ትሪክ ወደ ድል ተመልሷል

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአንድ ሳምንት እረፍት በኋላ በሁለተኛዋ አስተናጋጅ ከተማ ጅማ ሲጀምር ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማን 3-2 በማሸነፍ ከደርቢው ሽንፈት አገግሟል።

ጅማዎች ከሰበታ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው የመጀመሪያ አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ከድር ኸይረዲን እና ብዙዓየሁ እንዳሻውን ከጉዳት መልስ በተመስገን ደረሰ እና ሳዲቅ ሴቾ ምትክ ሲያሰልፉ በጊዮርጊስ በኩል በሸገር ደርቢ የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነው ፓትሪክ ማታሲን በለዓለም ብርሀኑ እንዲሁም የአብስራ ተስፋዬን በሀይደር ሸረፋ ምትክ ጨዋታውን አስጀምረዋል።

ጀማዎች ጨዋታውን በመልካም ሁኔታ የጀመሩበት ጎልን ያስቆጠሩት ጨዋታው ብዙም ሳይገፋ ነበር። በ6ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ወደፊት ለማቀበል የሞከረው ኳስ ተቋርጦ ሮባ ወርቁ ጋር ደርሶ አጥቂው አክርሮ በመምታት በግሩም ሁኔታ ከመረብ ጋር ማገናኘት ችሏል።

ከጎሉ በኋላ ጅማዎች ሙሉ ለሙሉ ከኳስ ጀርባ በመሆን ጥብቅ መከላከልን ምርጫቸው ሲያርጉ በፈረሰኞቹ በኩል ኳስን ተቆጣጥረው ክፍተት በመፈለግ የማጥቃት ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ቆይተው በ35ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ በሳጥን ውስጥ በወንድማገኝ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ጌታነህ ከበደ ወደ ጎልነት ቀይሮ አቻ መሆን ችለዋል።

ከሁለት ደቂቃ በኋላ ጅማዎች በድጋሚ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት ወርቃማ ዕድል ቢያገኙም መጠቀም አልቻሉም። እንደመጀመርያው ሁሉ ከቅብብል ስህተት ያገኙትን ኳስ ሙሉቀን ታሪኩ አግኝቶት የለዓለምን አቋቋም ተመልክቶ ወደ ጎል የላከው ኳስ በቀላሉ መክኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች የአሰላለፍም ሆነ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የበለጠ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥቦች አግኝተዋል። በመጀመርያዎቹ አስር የአጋማሹ ደቂቃዎችም በአቤል ያለው፣ ጋዲሳ፣ ጌታነህ እና በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ጨዋታ ያደረገው ሳላዲን ሰዒድ አማካኝነት ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በ58ኛው ደቂቃ ከአቤል ያለው የተሻማውን የማዕዘን ምት ጌታነህ ከበደ በግኖባሩ ገጭቶ ፈረሰኞቹን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ጊዮርጊሶች ወደፊት በማምራት የጎል አጋጣሚ መፍጠራቸውን ቀጥለው ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ከሄኖክ አዱኛ የተሻገረውን ኳስ ጌታነህ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሐት-ትሪክ ሰርቷል።

ከጨዋታው የሚፈልጉትን ያገኙ የሚመስሉት ጊዮርጊሶች ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በመጠኑ ቢቀዛቀዝም በጋዲሳ እና ተቀይረው በገቡት አዲስ ግደይ እና ሀይደር ሸረፋ አማካኝት መልካም ዕድሎች መፍጠር ችለዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የጊዮርጊስን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ተቸግረው የታዩት ጅማዎች በአንፃሩ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ወጣቱ ቤካም አብደላ በ83ኛው ደቂቃ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂውን በእርጋታ አልፎ እጅግ ድንቅ ጎል ካስቆጠረ በኋላ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጊዮርጊስን ጫና ውስጥ መክተት ችለው ነበር። ሆኖም ተጨማሪ ጎሎች ሳይቆጠሩ ጨዋታው በጊዮርጊስ 3-2 አሸናፊነት ተገባዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ