የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 2-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ረፋድ ላይ የተከናወነው የሰባተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከተጋጣሚ አሰልጣኞች ተከታዮቹም አስተያየቶች ተቀብሏል።


አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው…

የተሻለ ልምድ ካለው ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው። ያሳደግኳቸው ተስፋ ሰጪ ተጫዋቾቼን የተመለከትኩበትም ነበር። ከባድ ጨዋታ ነበር። ሰውም እንደዚህ ዓይነት ፉክክር የጠበቀበት ጨዋታ አልነበረም። ብንሸነፍም ተጫዋቾቼ ላይ ተስፋ ሰጪ ነገር አይቻለሁ።

ከመጀመሪያው ግብ በኋላ ቡድኑ ስለማፈግፈጉ…

በ4-5-1 ኳስ ከኃላ በመጀመር ለመጫወት ነበር የፈለግነው። ምክንያቱም የጊዮርጊስን የመሀል ሜዳ ለመስበር ተጫዋቾች መሀል ላይ ኳስ እንዲቀሙ የሚፈለገውን ነገር አድርገናል ፤ ያም ተሳክቶልን ነበር። ሆኖም ከዕረፍት በፊት በፍፁም ቅጣት ምት ተቆጠረብን። በአጠቃላይ ለሚቀጥለው ጨዋታ ለመሻሻል የሚደረገውን ሁሉ እናደርጋለን።

ስለሁለተኛው ግብ…

እንግዲህ ወደ ጅማ ከመጣሁ በኃላ ያወጣሁት ልጅ ነው። አሁንም ተቀይሮ ሲገባ በቢጫ ቴሴራ ነው። ቴሴራ ወጥቶለት ምናምን እንዳይመስላችሁ። እና ከጅማ እነደዚህ ዓይነት ልጆች ማውጣት ነው የእኔ ትልቁ ነገር። ቡድኑን በተረጋጋ መንገድ ለማስቀጠልም የምችለውን ሁሉ አደርጋለው።

አሰልጣኝ ማሂድ ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች…

ለተጫዋቾቹ ምስጋና ይገባቸዋል። ተቀያያሪ የሆነ አቀራረብ ነበረን። በመጀመሪያውም በሁለተኛውም አጋማሽ ቀይረነዋል። ለሦስተኛ ጊዜም ለውጥ አድርገን ነበር። ከመመረታ ተነስተንም 3-1 መሆን ችለናል። ይህንን የቡድኑን መነሳሳት ወደ ሌሎቹም ጨዋታዎች ይዘን መሄድ ይገባናል።

እስካሁን በብዛት ያልተጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች ስለማስገባታቸው

በቀጣይ የተጨናነቀ መርሐ-ግብር ነው የሚጠብቀን ፤ በአንድ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎችን ማከናወን ይኖርብናል። በመሆኑም ሳላሀዲን ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ እገዛ አድርጓል ፣ አዲስም ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ ተንቀሳቅሷል የዓብስራም በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጓል። በአጠቃላይ እንደቡድን ተጫውተን የዛሬውን ውጤት አሳክተናል።

ስለጌታነህ ከበደ የዕለቱ ብቃት…

ስለእሱ ምን ማለት እችላለሁ ? ጌታነህ ባለፉት ዓመታትም የተረጋገጠለት ግብ አስቆጣሪ ነው ፤ ቡድኑንም ይመራል። ነገር ግን አሁንም የምደግመው ውጤቱ የቡድን መሆኑን ነው። ጌታነህ ግቦችን አስቆጥሯል ፤ ግን አማካይ ላይ ካልሰራን ፣ መከላከል ላይ ካልሰራን ፣ በመስመሮች ካልሰራን ውጤቱ አይመጣም። ለምሳሌ እንዳልከው ሳልሀዲን ተቀይሮ ገብቶ ልዩነት ፈጥሯል። ስለዚህ እውነት ነው ጌታነህ በምርጥ ብቃት ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል። ቡድኑ ግን እንደአጠቃላይ ሦስት ነጥቦችን አሳክቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ