የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0 0 ሰበታ ከተማ

ያለግብ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የድቻ እና የሰበታ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ይህንን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለጨዋታው

ከዝግጅታችን ማነስ አንፃር ብዙም በአጨዋወት ፍልስፍናችን ላይ መሰረት አድርገን አልተጫወትንም ፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ይሻል ነበር ብዬ አስባለሁ። በሁለተኛው አጋማሽ የኛ ተጫዋቾች ላይ መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት መውረድ ታይቷል። ይህ ደግሞ ካልሰራህ ሊከሰት የሚችል ነገር ነው። ከዚህ በተረፈ ግን ተጫዋቾቹ የሰጠኋቸውን ታክቲክ ተግብረው ወጥተዋል። ለዚህ ጨዋታ ስንመጣ ከዝግጅታችን አንፃር ማሸነፍ ካልሆነ ደግሞ ነጥብ ይዘን ለመውጣት ስለነበር እንደዝግጅታችን የምንፈልገውን ነገር አሳክተን ወጥተናል ማለት እችላለሁ።

ቡድኑ ፈጣሪ ተጫዋቾችን ስለመቀነሱ እና ጥንቃቄ ላይ ስለማተኮሩ

በትክክል የጥንቃቄ ጨዋታ ነው የመረጥኩት። ምክንያቱም ያልተዘጋጀ ቡድን ልክ እንደተዘጋጀ ቡድን ደፍሮ መንቀሳቀስ ስለሌለበት ማለት ነው። ስለዚህ ትልቁ ስራችን የነበረው በተቻለ መጠን ግብ እንዳይቆጠርብን ማድረግ ነው። ከዚያ በኋላ ግን በምናገኛቸው አጋጣሚዎች እና ቀይረን ባስገባናቸው አጥቂዎች ለመጫወት ነበር። ያው አንድ አጥቂ ሳልቀንስ ቀርቻለሁ። ከአካል ብቃት ጋር ተያይዞ ቢያድግልኝ በጉዳት ነው የወጣብን። እንደገና ደግሞ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አብዱልባስጥም ተጎድቷል። ‘ቀይረኝ !’ እያለ ‘ቅያሪ ጨርሻለሁ’ ብዬው ነው። ከዛ አንፃር የመጀመሪያው ስራችን ግብ እንዳይገባብን ማድረግ ነበር። ያንን አሳክተን ወጥተናል ማለት እችላለሁ እንጂ ፈጣሪ ተጫዋቾችን ቀንሰን ነው የገባነው።

አሰልጣኝ ዘላለም ማቲዮስ – ወላይታ ድቻ

ከጥንቃቄ አንፃር ቡድኑ ያሰበውን ስለማሳካቱ

አዎ ! ያሰብኩትን አሳክቻለሁ ብዬ ነው የማስበው ፤ የጎል ዕድሎችንም ፈጥረናል። አምስት ጨዋታዎችን ተሸንፈን ነው የመጣነው። ያንን ሥነ-ልቦና ለመገንባት አንድ ነጥብ ማግኘት አለብን የሚለውን ሀሳብ አሳክቻለሁ።

እኔ ያሰብኩትም እንደዛ ነበር። ኳሶችን በመልሶ ማጥቃት በመጣል የግብ ዕድሎችን መፍጠር ነበር። ያንን ደግሞ ከሞላ ጎደል ተጫዋቾቼ በሚገባ ተግብረውልኛል።

የቡድኑ አጨዋወት የአዲሱን አሰልጣኝ አቀራረብ የሚያሳይ ስለመሆኑ

እሱን አላውቅም። የእሱ ፍልስፍና አለ ፤ በእሱ ፍልስፍና ነገሮችን የምናይ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ