ባህር ዳር እና ሀዋሳን በሚያገናኘው ጨዋታ ላይ ያተኮረው ዳሰሳችንን እንዲህ አሰናድተናዋል።
ከሰባተኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሳቢ ፉክክርን ሊያስመለክቱን ከሚችሉ ጨዋታዎች ውስጥ አንዱ ይህ ግጥሚያ ይሆናል። በማጥቃት ሀሳብ ውስጥ ሆነው ወደ ጨዋታው እንደሚመጡ የሚጠበቁት ሁለቱ ቡድኖች በወጣት አሰልጣኞቻቸው እየተመሩ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
እስካሁን ተከታታይ ድሎችን ማሳካት ያልቻለው ባህር ዳር ከተማ ከእንደነገ ዓይነት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን አሳክቶ አሸናፊነቱን ማስቀጠል እና ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል። በነገው ጨዋታ የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን ከድሬዳዋ ጨዋታ የተለየ አጥቅቶ የሚጫወት ተጋጣሚን የሚያገኝ በመሆኑ ከተጋጣሚው ክፍተቶች በመነሳት የማጥቃት አማራጮቹን ሊያሰፋ እንደሚችል ይጠበቃል። በተለይም ደካማ እየሆነ የመጣበትን የሜዳውን ስፋት የመጠቀም ችግሩን ከሀዋሳ የመስመር ተመላላሾች የወደፊት እንቅስቃሴ በመነሳት ሊጠቀም የሚችልበት የጨዋታ ዕቅድ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል።
በአመዛኙ በፍፁም ዓለሙ የሜዳው ቁመት ያተኮረ እንቅስቃሴ ላይ ያመዘነ የማጥቃት አማርጩ ተገማች እያደረገው መምጣቱ ግን ለባህር ዳር ለነገውም ጨዋታ ፈታኝ የሚሆንበት ጉዳይ ነው። በውድድሩ ጅማሮ ላይ የነበረው የመስመር ተከላካዮች ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ ፣ የፊት አጥቂው የተሳካ የአማካይ መስመር ግንኙነትን መልሶ በነገው ጨዋታ ማግኘት ለቡድኑ ወሳኝ ይሆናል። እዚህ ላይ በሁለት ጨዋታዎች ከመስመር የመነሳት ኃላፊነት የተሰጠው አማካይ ሆኖ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተስተዋለው አህመድ ረሺድ ሚና ዳግም ለበድኑ መፍትሄ ይሆን እንደሆንም ከጨዋታው የምናየው ይሆናል።
ራሱን ፈልጎ ያገኘ የሚመስለው ሀዋሳ ከተማ ከጨለማ ጉዞ ያላቀቁትን ሰባት ነጥቦች በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ማሳካት ችሏል። ቡድኑ ከጅማ በተለይ ደግሞ ድቻ ጋር ያደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ የታየበት ተለዋዋጭነት እና የማጥቃት አማራጬቹ መስፋት ለነገው ፍልሚያ በብዙ የሚያግዘው ይሆናል። በአቀራረቡ ተቀያያሩነት ለተጋጣሚው በቀላሉ ያለመገመቱ ነገር ግን በቡድኑ መዋቅር ላይ የውህደት ችግር እንዳያመጣ ተዘጋጅቶ መቅረብ የግድ ይለዋል። ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ በጎ ፈተና የሚሆነው ጉዳይም በድንገት አሰላለፍ ውስጥ ገብተው ድንቅ የነበሩ ተጫዋቼችን ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ጋር አፎካክሮ የማሰለፉ ነገር ይሆናል።
ያልተጠበቁ የተጨዋቾች ለውጦች በማድረግ እና ሳይታሰብ የ 3-5-2 አደራደርን በመጠቀም ወላይታ ድቻን በሙሉ ብልጫ ማሸነፉ ለሀዋሳ በራስ መተማመኑን ከፍ ከማድረግ ያለፈ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። በዚህም ምንም እንኳን የነገ ተጋጣሚው ጠንከር ያለ በመሆኑ የሚያገኙት ክፍተት ብዙ ላይሆን ቢችልም የሀዋሳ መስመር ተመላላሾች የነበራቸው የማጥቃት ተሳትፎ ከተደገመ ለቡድኑ የጎል ዕድሎችን የመፍጠር አቅማቸው ከፍ ያለ ነው። ፊት መስመር ላይም የብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ ጥምረት ለጨዋታ አቀራረቡ የተመቸ ሆኖ ታይቷል። ሀዋሳ በተመሳሳይ አኳኋን ወደ ሜዳ ከገባ እና በድጋሚ ውጤታማ ከሆነ ግን በቀጣይ አዘውትሮ 3-5-2ን የመጠቀም አዝማሚያ ሊያሳይ እንደሚችል ይገመታል።
ባህር ዳር ከተማዎች አቤል ውዱ እና ሳምሶን ጥላሁን ልምምድ የጀመሩላቸው ቢሆንም ነገ በቋሚነት የመሠለፋቸው ነገር አልለየለትም። ከዚህ ውጪ የሆድ ህመም ከገጠመው በረከት ጥጋቡ ውጪ የሁለት ቢጫ ሰለባ የነበሩት ወሰኑ ዓሉ እና ምንይሉ ወንድሙን ጨምሮ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ሆናል። ሀዋሳ ከተማዎች በወረቀት ጉዳዮች የድቻው ጨዋታ ያለፈውን ጋብርኤል አህመድን ግልጋሎት መልሶ የሚያገኝ ይሆናል። ከወጣቱ አጥቂ ሀብታሙ መኮንን በቀርም በቡድኑ ውስጥ የተሰማ ሌላ የጉዳት ዜና የለም።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱንም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት 1-1 እና 0-0 አጠናቀዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)
ሶሆሆ ሜንሳህ
ወንድምአገኝ ማዕረግ – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ
ዳንኤል ደርቤ – ኤፍሬም ዘካርያስ – ጋብርኤል አህመድ – ወንድምአገኝ ኃይሉ –ደስታ ዮሐንስ
ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ
ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)
ሀሪሰን ሄሱ
ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ
ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አፈወርቅ ኃይሉ
ዜናው ፈረደ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ
ባዬ ገዛኸኝ
© ሶከር ኢትዮጵያ