ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ድንቅ ጎል ያስቆጠረው ተስፈኛ ወጣት ይናገራል

የአዲሱ ትውልድ ተጫዋቾችን እየተመለከትን በምንገኝበት የዘንድሮ ዓመት ውድድር በዛሬው ዕለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ አስደናቂ ጎል ካስቆጠረው ተስፈኛ ወጣት ቤካም አብደላ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ጅማ ከተማ ቁጠባ በሚባል አካባቢ ተወልዶ አድጓል። በአሰልጣኝ ጋሻው ፕሮጀክት እግርኳስን እየተጫወተ ለሦስት ዓመት ቆይታ አድርጓል። (በነገራችን ላይ አሰልጣኝ ጋሻው እንደ ሳላዲን ሰዒድ ያለ ታላቅ ተጫዋች ያፈራ በርካታ ትውልዶችን መፍጠር የቻለ ክብር ሊቸረው የሚገባ አሰልጣኝ ነው።) ቤካም አብደላ የአካዳሚ እድል አግኝቶ አሰላ ወደሚገኘው ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ለአራት ዓመታት ሰልጥኖ መጨረስ ችሏል። በ2012 ጅማ አባ ጅፋርን በመቀላቀል ባህር ዳር ላይ በተደረገ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ብቻ ተቀይሮ በመግባት የመጫወት ዕድል አግኝቷል። በዛሬው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ ተቀይሮ በመግባት በአስገራሚ ሁኔታ በ83ኛው ደቂቃ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂውን በተረጋጋ ሁኔታ አልፎ እጅግ ድንቅ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ማስቆጠሩ እና የመጠርዬ ስሙን ለየት ማለት ተከትሎ ዛሬ የመነጋገርያ ርዕስ ሆኖ ውሏል።

ወደ ፊት በቂ የመጫወት ዕድል ካገኘ የተሻለ ነገር ማሳየት እንደሚችል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየው ቤካም ስለ መጠርያ ስሙ፣ ስለ ዛሬው ጎል እና በቀጣይ ስለሚያስበው በተከታዩ መልኩ አጋርቶናል።

“ቤካም የሚለውን ስም ያወጣልኝ አባቴ ነው። ያው እግርኳስን ስለሚወድ እና የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊ በመሆኑ በእንግሊዛዊው ተጫዋች ቤካም ስም የኔን መጠሪያ አውጥቶልኛል። አባቴ እግርኳስ ተጫዋች እንድሆን ትልቅ እገዛ ሲያደርግልኝ ቆይቷል።

“ሁሌም ለእንዲህ አይነት ቀን ራሴን እያዘጋጀሁ እጠብቅ ነበር። አንድ ቀን የመሰለፍ ዕድል አገኛለሁ ወይም ተቀይሬ እገባለው የሚል እምነት በውስጤ ነበር። ዛሬ አሰልጣኝ ጳውሎስ ተነስተህ አሟሙቅ ሲለኝ እጅግ ደስ ብሎኝ ነው የተነሳሁት። ለኔ ተቀይሮ ገብቶ መጫወቱ በራሱ በቂ እድል ነው። በጨዋታው ጎል አስቆጥራለሁ የሚል ፍፁም ግምት አልነበረኝም። ኳሱ እግሬ ሲገባ ተረጋግቼ መወሰን ያለብኝን ወስኜ ጎል አስቆጥሬያለው እንጂ ጎል አገባለው ብዬ አላሰብኩም። ይህች ጎል ለነገ የእግርኳስ ህይወቴ ትልቅ መነሳሻ ነው የሚሆነኝ የበለጠ ጠንክሬ እንይሰራ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው።

” ጎሉን በመልሶ ማሳያ ሆቴል ከገባው በኃላ ደጋግሜ ሳየው ማመን አቅቶኛል። አስበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው። ተከላካዮቹ ግብጠባቂው ልምድ ያላቸው ናቸው። እነርሱን በዚህ መልኩ አልፌ ይህን ጎል ማስቆጠር በጣም አስደሳች ነው። ምንም አላመንኩም ነበር። ጎሉን አግብቼ ደስታዬን የገለፅኩበት መንገድ ራሱ ደግሜ ሳየው አስገርሞኛል።

“አሰልጣኝ ጋሻው ለኔ ትልቅ ባለ ውለታዬ ነው። ሁልጊዜም ጠንክሬ ጥሩ ተጫዋች እንድሆን ይመክረኛል። ሳላዲን ሰዒድን እንደማሰልጠኑ ሁሌም እንደ እርሱ ዲሲፕሊንድ ሆኜ እንድወጣ ይነግረኛል። ወደፊት ብዙ ነገር አስባለሁ። በሀገሬ መጫወት እና የብሔራዊ ቡድን ማልያ ለብሶ መጫወት ትልቁ ህልሜ ነው። አሁን ገና እየጀመርኩ ነው፤ ከዚህ በኃላ ከእኔ ብዙ ነገር ይጠበቃል። ሳላዲን እና ጌታነህ የደረሱበት ደረጃ እንደምደርስ ተስፋ አደርጋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ