ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

የሲዳማ እና ድሬዳዋን ጨዋታ የተመለከቱ ሀሳቦችን እንደሚከተለው አንስተናል።

ከሽንፈት በተመለሱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ይህ ጨዋታ በቶሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ውስጥ እንደመደረጉ ጥሩ ፉክክርን ሊያስመለክት ቢችልም የቡድኖቹ የተዳከመ የፊት መስመር ግን ከጨዋታው በርካታ ግቦችን እንዳንጠብቅ የሚያደርገን ጉዳይ ነው። እስካሁን ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ ምንም ግብ ያላገኘው ሲዳማ በዚህ ረገድ ይበልጥ ሊቸገር የሚችል ሲሆን ወጥም ባይሆን ከእነ ሙኸዲን ሙሳ እና አስቻለው ግርማ ግቦችን ሲያገኝ የሚስተዋለው ድሬዳዋ ከተማም ከአጨራረስ ችግር ሙሉ ለሙሉ ነፃ አይደለም። በዚህ ረገድ በወረቀት ጉዳዮች እና በተደታታቢ ጉዳቶች የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ግልጋሎት በሚፈልጉት መጠን የማያገኙት ሁለቱ ቡድኖች ምን መፍትሄ ይዘው እንደሚመጡ ከጨዋታው የምንጠብቀው ጉዳይ ይሆናል።

አማካይ ክፍል ላይ ድሬዳዋ በኤልያስ ማሞ ሲዳማ ደግሞ በዳዊት ተፈራ ላይ ተመርኩዘው የሚያደርጉት ፍልሚያ ሌላው ትኩረት የሚስብ ነጥብ ይሆናል። ሁለቱ ፈጣሪ አማካዮች ከተጋጣሚዎቻቸው ተከላካይ አማካዮች የሚገጥማቸው ፈተና ሌላኛው የጨዋታው ተጠባቂ ጉዳይ ነው። በአማካይ ክፍል የውህደት ደረጃ እና በቁጥርም ብልጫ ሊወስድበት የሚችለው ሲዳማ በዚህ ረገድ ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹም በቂ እገዛ ማግኘት የሚኖርበት ይመስላል። ሲዳማ በወልቂጤው ጨዋታ ድንቅ የነበረው ጊት ጋትኮችን ወደ ተጠባባቂነት አውርዶ በፋሲሉ ጨዋታ የታየበት የኋላ መስመር ክፍተቱ ሌላው በዚህ ጨዋታ ሊታረም የሚገባው ነጥብ ነው። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ በባህር ዳሩ ጨዋታ ሙሉ በሙሉ በመሀል ተከላካዮች ተዋቅሮ የማጥቃት ተሳትፎው እጅግ የተዳከመ የነበረው የኋላ ክፍል ለውጦች ተደርገውበት ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ገፍቶ የመጫወት የተሻለ ድፍረት ሊታይበት እንደሚችል ይገመታል።

ሲዳማ ቡና በአዲስ አበባ ጨዋታዎች ላይ ጉዳት የገጠማቸው አዲሱ አቱላ እና ይገዙ ቦጋለን ግልጋሎት አሁንም የማያገኝ ሲሆን ሌላው ወሳኝ የቡድኑ አጥቂ ጫላ ተሺታም እንዲሁ ለጨዋታው አይደርስም። በአንፃሩ ከመጀመሪያው የቡድኑ ጨዋታ በኋላ ዳግም ያልተመለከትነው ማማዱ ሲዲቤ ከግል ጉዳይ በኋላ መመለስ ለሲዳማ መልካሙ ዜና ሆኗል። ከጉዳት የተመለሱት ሱራፌል ጌታቸው እና ምንያምር ጴጥሮስን የመጠቀም ዕድል ያለው ድሬዳዋ ከተማ የኢታሙና ኬይሙኒ እና ጁኒያስ ናንጄቤ የወረቀት ጉዳይ አለመጠናቀቅ ለነገው ጨዋታ እንዳይደርሱ እክል እንደሆነበት ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ14 ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና በ7 ድል ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ 1 ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ግንኙነቶች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በ14 ግንኙነቶች ሲዳማ 14 ጎሎች ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 6 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2)

ፍሬው ጌታሁን

ምንያምር ጴጥሮስ – ፍቃዱ ደነቀ – በረከት ሳሙኤል – ዘነበ ከበደ

ዳንኤል ደምሴ

ሱራፌል ጌታቸው – ኤልያስ ማሞ – አስቻለው ግርማ

ሙኽዲን ሙሳ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ጊት ጋትኮች – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ዮሴፍ ዮሐንስ

ተመስገን በጅሮንድ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ