የፕሪምየር ሊጉ የውድድር ዘመን አጋማሽ እረፍት መቼ እንደሆነ ታወቀ

በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ የሚገኘው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን አጋማሽ ዕረፍት ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ እንደሆነ ታውቋል።

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በሁለተኛ አስተናጋጅ ከተማ የሆነችው ጅማ ከተማ ከጥር ሰባት ጀምሮ እስከ የጥር 28 ቀን ድረስ ከሰባተኛው እስከ አስራ አንደኛው ሳምንት ድረስ ጨዋታዎቹን ካደረጉ በኋላ ቡድኖቹም ለ13 ቀናት እረፍት ካደረጉ በኃላ ከየካቲት 12 ጀምሮ አስራ ሁለተኛ ሳምንት በባህርዳር እንደሚጀምር ታውቋል።

ከዚህ ቀደም የመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ እንደተጠናቀቀ የተወሰኑ ጊዜያት እረፍት ተሰጥቶ ሁለተኛው ዙር እንደሚጀምር የሚታወቅ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ቡድኖች በአንድ ከተማ ተሰባስበው የሚጫወቱ በመሆኑ የቀደመው አሰራር ላይ ለውጥ እንዲኖር ያደረገ ይመስላል። ከጅማ በመቀጠል አስቀድሞ በወጣው መርሐግብር ለባህር ዳር ከተማ ውድድሩን ለማስተናገድ የተሰጣት 12ኛ እና 13ኛ ሳምንት ጨዋታ ብቻ ቢሆንም አወዳዳሪው አካል ይህ በቂ አለመሆኑን በመገንዘብ ከ12ኛ እስከ 16ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ባህር ዳር ላይ እንዲካሄድ ማሻሻያ በማድረግ ወስኗል። በዚህም መሠረት ቡድኖቹ በከተማው ተቀምጠው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችን እንዲጨርሱ በማሰብ ምንም እንኳ 13ኛው ሳምንት የዓመቱ ማጋመሻ ቢሆንም በከተማው የሚደረጉ ጨዋታዎች ከየካቲት 12 ጀምሮ እስከ መጋቢት 3 ድረስ ከተከናወኑ በኋላ እረፍት እንደሚኖር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዓመቱ አጋማሽ እረፍት ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ጋር ተደምሮ ለሦስት ሳምንታት (21 ቀናት) የሚቆይ ሲሆን ከእረፍት መልስ መጋቢት 24 ላይ በ17ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ስታዲየም ላይ የሚቀጥል ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ