ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ

የሰባተኛው ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር የሆነውን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ቃኝተነዋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጡትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የሚባል ዓይነት ነው። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች አራት ድሎችን ማሳካት ከቻሉ ቡድኖች መካከል የሆኑት ሀዲያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ያላቸውን ገዞ ለማስቀጠል ይፋለማሉ። በስድስቱ የጨዋታ ሳምንታት ጥቂት ግብ ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕናን በርከት ያሉ ግቦች በማስቆጠር ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ፋሲል ማገናኘቱም የጨዋታውን ተጠባቂነቱ ከፍ ያደረገ ሌላው ጉዳይ ሆኗል።

ከአራት ድሎች በኋላ ከወልቂጤ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አሁን ባለው የደረጃ ሰንጠረዥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአምስተኛ ደረጃ በላይ ካለ በድን ጋር ይገናኛሉ። ወጥ ጉዞ ማድረግ ዳገት በሆነበት ሊጋችን የሀዲያ አራት ተከታታይ ድሎች ያላቸው ቦታ ትልቅ ቢሆንም ከእስካሁኑ ጉዞው ከባዱን ፈተና ነገ የሚጋፈጥ መሆኑ ግን እሙን ነው። በቀላሉ ጎላቸውን የማያስደፍሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግብ በማስቆጠሩም በኩል ከዳዋ ሆቴሳ ጥገኝነት ተላቀው በሳሊፉ ፎፋናም ተከታታይ ግቦችን ማግኘታቸው ከቢስማርክ አፒያ መልካም አቋም ጋር ተዳምሮ የፊት መስመራቸውን ጠንካራ ያደርገዋል። ቡድኑ ከሚያደርገው ተደጋጋሚ የቅርፅ እና የተጫዋቾች ለውጥ አንፃር ግን የአማካይ ክፍሉ ውህደት እንደተጋጣሚው ፋሲል ተመሳሳይ ክፍል ላይሆን መቻሉ ለነገው ጨዋታ እንደስጋት የሚወሰድ ነው። በዚህ ረገድ ሆሳዕና በሳምንቱ አጋማሽ ዮናስ ገረመውን በእጁ ማስገባቱ አማራጬቹን ሊያሰፋለት ይችላል።

ሲዳማን በመርታት ለዚህ ጨዋታ የደረሰው ፋሲል ከነማ በጨዋታዎች መሀል የሚታይበት መቀዛቀዝ ሙሉ ለሙሉ ተወገደ ባይባልም ውጤታማ ጉዞ እያደረገ እንደሆነ ግን መካድ አይቻልም። በተለይም ባለፉት ተከታታይ አራት ጨዋታዎች ግብ እያስቆጠረ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም ለቡድኑ ስኬት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ነገም ግዙፉ አጥቂ ከጠንካራው የሀዲያ ሆሳዕና የኋላ ክፍል ተሰላፊዎች ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ትኩረትን የሚስብ ይሆናል። በሌላ ጎኑ ግን የቡድኑ ዋነኛ የጎል ምንጭነት በሙጂብ ላይ የተመረኮዘ መስሎ መታየቱ እና የግብ አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ ያሉት ከቆሙ ኳሶች ፣ ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ስህተት እና ከግል ጥረቶች መሆኑ በአፄዎቹ በኩል በደካማ ጎንነት የሚነሳ ነው። ከዚህ በተለየ በድኑ ጊዮርጊስን ካሸነፈበት የመክፈቻ ጨዋታው በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱ ወደ ነገው ጨዋታ ይዞት የሚሄደው ጠንካራ ጉኑ ነው።

በነገው ጨዋታ ከሚጠበቁ ፍልሚያዎች ውስጥ የመስመር ጥቃቶች ተጠቃሽ ናቸው። በተደጋጋሚ የተጨዋቾች አደራደር ለውጥ የሚያደርገው ሀዲያ ሆሳዕናም ሆነ በተለይም በግራ መስመር ካደለ ጥቃት የግብ ዕድሎችን የሚፈጥረው ፋሲል መሀል ለመሀል ከሚደረጉ ጥቃቶች ይልቅ ሁለቱን መስመሮች የመጠቀም ዝንባሌ ሊታይባቸው ይችላል። በተለይም የዳዋ ሆቴሳ እና ሽመክት ጉግሳ እንቅስቃሴ ለቡድኖቻቸው የመጨረሻ አጥቂዎች ወሳኝ እንደሚሆኑ ሲጠበበቅ አምሳሉ ጥላሁን እና ሱለይማን ሀሚድም የተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ይገመታል። ከመስመር እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ መሀል ላይ ካሉት እንደ ሱራፌል ዳኛቸው እና ካሉሻ አልሀሰን ዓይነት ባለተሰጥኦ አማካዮች አንፃርም የቡድኖቹ ተከላካይ አማካዮች በሜዳው ቁመትም ሆነ ስፋት ስራ ሊበዛባቸው እንደሚችል ይታሰባል።

ሀዲያ ሆሳዕና በዚህ ጨዋታ ቅጣቱን ከሚያጠናቅቀው ግብ ጠባቂ መሀመድ ሙንታሪ ውጪ በጉዳት የሚያጣው ሌላ ተጫዋች አይኖርም። በፋሲል በኩልም በሲዳማው ጨዋታ ግጭት ደርሶበት ቀዶ ጥገና ካከናወነው ሰዒድ ሀሰን ውጪ ቀሪው ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆን እንየው ካሣሁንም ከሆድ ህመሙ አገግሞ ለነገው ፍልሚያ ደርሷል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ተገናኘተው ፋሲል 3-0 ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያውን የሊጉን የእርስ በእርስ ጨዋታቸወን ያከናውናሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ደረጄ ዓለሙ

አይዛክ ኢሲንዴ – ተስፋዬ በቀለ – ቴዎድሮስ በቀለ

ሱሌይማን ሀሚድ – ካሉሻ አልሀሰን – ተስፋዬ አለባቸው – አማኑኤል ጎበና – ሄኖክ አርፌጮ

ሳሊፉ ፎፋና – ዳዋ ሆቴሳ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ

ሳሙኤል ዮሐንስ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሽመክት ጉግሳ

ሙጂብ ቃሲም


© ሶከር ኢትዮጵያ