“ሁለተኛ ሴት ልጄን የማገኝ በመሆኑ ይህን ለማሰብ ነው ደስታዬን የገለፅኩት” – ኤፍሬም አሻሞ

ኤፍሬም አሻሞ ዛሬ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ስለገለፀበት መንገድ ይናገራል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን 2-1 በረታበት ጨዋታ ኤፍሬም አሻሞ ተቀይሮ በመግባት ድንቅ ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ደስታውን የገለፀበት መንገድ ብዙዎችን አነጋግሯል። በሊጉ ለተለያዩ ቡድኖች እና በብሔራዊ ቡድን ሲጫወት የምናቀው ኤፍሬም አሻሞ ከመስመር እየተነሳ የሚፈጥራቸው የጎል እድሎች እና በሚያስቀቆጥራቸው ጎሎቹ ቢታወቅም ከምንም በላይ ጎል አስቆጥሮ ደስታውን የሚገልፅበት የተለየ መንገድ ብዙዎቹ ዘንድ የሚታወቅ የእርሱ መገለጫ ሆኗል። ዛሬም በጨዋታውን ልዩነት የፈጠረ ጎል ተቀይሮ በመግባት ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን የገለፀበትን መንገድ እና ተዛማች ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኤፍሬም አሻሞ ጋር ቆይታ አድርገናል።

” ጎሉን አግብቼ ደስታዬን የገለፅኩበት ሁኔታ… ከባለቤቴ በቅርቡ ሁለተኛ ሴት ልጄን የማገኝ በመሆኑ ይህን ለማሰብ ነው ደስታዬን የገለፅኩት። እግርኳስን በመጫወት ከማገኘው መዝናናት በመቀጠል ጎል አግብቼ ደስታዬን መግለፅ ሁልጊዜም ያዝናናኛል። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ጎል አግብቼ ፈገግታን በሚያጭሩ የተለያዩ አኳኋኖችነ ደስታዬን መግለፅ የምፈልገው። ተመልካቹ ወደ ሜዳ ሲገባ መዝናናትን ይፈልጋል። ስለዚህ ይሄን የማድረግ ልምድ አለኝ። በተለይ ደግሞ እንደ ዛሬው ዐይነት ጎል ሲቆጠር ደስታህን የምትገልፅበት መንገድ የተለየየ መዝናናትን የሚፈጥር መሆኑ ግድ ይላል። ይህ መለመድ መቀጠል አለበት። ሁሉም ተጫዋች የራሱ የሆነ የደስታ አገላለፅ ባህል ሊኖረው ይገባል። የኔ ደግሞ የሚለየው ራሴን በማዝናናት በመደነስ ወጣ ያላ ነገር በማሳየት ደስታዬን እገልፃለሁ። ወደፊትም በእኔ በኩል ይህን ድርጊቴን እቀጥላለሁ።

“ሀዋሳ በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ትንሽ ናቸው። ያም ቢሆን በጣም ደስ የሚል ፍላጎት ያለበት ቡድን ነው። ከዚህም በኃላ ከወጣቶቹ ብዙ ነገር የሚጠበቅ ነው። የበፊቱን ሀዋሳን ለመመለስ ከጓደኞቼ እና ከአሰልጣኛችን ጋር ያለንን አቅም አሟጠን ለመስጠት አስባለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ