ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የሰባተኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን በዚህ መልኩ አንስተናል።

አዲስ አበባ ላይ የነበሩትን የጨዋታ ሳምንታት በድል የጀመረው አዳማ በቀጣይ አራት ጨዋታዎች ግን አንድ ነጥብ ብቻ አሳክቶ ስድስተኛውን ሳምንት በማረፍ ነገ የጅማ ውድድሩን ወልቂጤን በመግጠም ይጀምራል። የአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ቡድን 13 የሚደርሱ ቀናትን በማረፉ ያሉበትን ችግሮች አርሞ የመመለስ ዕድል ያገኘ ይመስላል። እጅግ የሳሳው የቡድኑ የማጥቃት ክፍል አሁንም ከጉዳት ነፃ ባይሆንም ባሉት ተጫዋቾች ደካማ ጎኑን አስተካክሎ እንደሚመጣ ይታሰባል። እስካሁን በአንድ ጨዋታ ብቻ መረቡ አለመደፈሩም በንፅፅር ወጥነት ያለው የተጫዋቾች ምርጫ የነበረው የኋላ ክፍሉ ችግር ብቻም አይመስልም። በመሆኑም የነገው ጨዋታ ራሱን ደግሞ ማየት የቻለበትን አጋጣሚ ያገኘው አዳማ በቀጣይ ምን ዓይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል የሚጠቁመን ይሆናል።

እስካሁን አንድ ሽንፈት ብቻ የገጠመው ወልቂጤ ከተማም እንደተጋጣሚው አይሁን እንጂ አስደሳች የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ነው ማለት አይቻልም። አጠቃላይ እንደቡድን በተናጠልም በቁልፍ ተጫዋቾቹ ላይ የሚታየው አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቅዝ የሚለው አቋሙ ለውጤቱ መዋዠቅ መነሻ ይመስላል። ቡድኑ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማን ከረታ በኋላ በጊዜው አንድም ድል ባልነበረው ሲዳማ ቡና መረታቱን እዚህ ላይ ማስታወስ የግድ ይላል። ነገም የተጋጣሚውን ድክመት ተመልክቶ ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን ጨዋታውን መጀመር ዋጋ ሊያከፍለው ይችላል። ብዙም ግቦችን ሲያስተናግዱ የማይታዩት ወልቂጤዎች ባለፈው ጨዋታ ከሄኖክ አየለ ያገኙት ግብ ከፊት አጥቂ ያገኙት ቀዳሚው ግብ ሆኗል። በዚህ ረገድ ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ለውጥ ሲደረግበት የሚታየው የቡድኑ ፊት አውራሪነት በሄኖክ ምላሽ ማግኘቱ ነገ የሚታይ ይሆናል። ጨዋታው ቡድኑ በሳምንቱ አጋማሽ ያስፈረመው ያሬድ ከበደን የመሰለፍ ዕድል በመስጠት በቦታው ያለበትን ችግር ለመፍታት የሚሞክርበትም ሊሆን ይችላል።

የአዳማ ከተማዎቹ አብዲሳ ጀማል እና ሱለይማን መሀመድ ከጉዳታቸው አገግመው ቀለል ያለ ልምምድ መጀመራቸው ለቡድናቸው መልካም ዜና ሲሆን በወልቂጤ በኩልም ከአሳሪ አልመሀዲ ቅጣት በቀር ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑን ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኘነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ሁለት ዙሮች በአዳማ የ1-0 እና የ2-0 አሸናፊነት የተጠናቀቁትን ጨዋታዎች ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች ነገ የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ዳንኤል ተሾመ

ታፈሰ ሰረካ – ደስታ ጌቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ

ሙጃይድ መሐመድ – ደሳለኝ ደባሽ

ፍሰሀ ቶማስ – በቃሉ ገነነ – የኋላእሸት ፍቃዱ

አብዲሳ ጀማል

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ሥዩም ተስፋዬ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሴ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ፍሬው ሰለሞን – ሄኖክ አየለ – ያሬድ ታደሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ