ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ወደ ድል ተመልሷል

በርካታ ክስተቶች የተስተናገዱበት የሰበታ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሰበታዎች ለዛሬው ጨዋታ ሦስት ለውጦች አድርገው በመቅረብ ፍፁም ገብረማርያም፣ ቡልቻ ሹራ እና መሳይ ጳውሎስን በእስራኤል እሸቱ ፣ ታደለ መንገሻ እና ቢያድግልኝ ኤልያስ ምትክ ተጠቅመዋል። ባህር ዳሮች በበኩላቸው የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በሀሪስተን ሄሱ ፣ ሚኪያስ ግርማ ፣ አፈወርቅ ኃይሉ ፣ ግርማ ዲሳሳ እና ባዬ ገዛኸኝ ምትክ ፅዮን መርዕድ ፣ ሳሙኤል ተስፋዬ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ወሰነ ዓሊ እና ምንይሉ ወንድሙ ጨዋታውን ጀምረዋል።

በባህር ዳሮች የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታው ግልፅ የጎል ዕድሎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ባይስተዋሉበትም በ14ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረን ኳስ ፋሲል ገብረሚካኤል በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ ወሰኑ ዓሊ አግኝቶ ወደ ጎል ሲመታ ዳንኤል ኃይሉ ደርሶ ተደርቦ ያወጣበት ኳስ የጣና ሞዶቹን ቀዳሚ ለማድረግ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከሙከራዎች ይልቅ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመውሰድ ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች በበዙበት እና ጥፋቶች በበረከቱበት የመጀመርያው አጋማሽ በሰበታዎች በኩል በቶሎ ቅያሪ ለማድረግ ያስገደደ ጉዳት ፉአድ ፈረጃ አጋጥሞት ገና በአስረኛው ደቂቃ በቃልኪዳን ዘላለም ተቀይሮ ወጥቷል።

በጨዋታው ቀጣዩን ጥሩ የጎል አጋጣሚ የተመለከትነው በ37ኛው ደቂቃ ሲሆን ፍፁም ዓለሙ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል መትቶ ፋሲል ያወጣበት የሚጠቀስ ነው። ካለፉት ጨዋታዎች በተሻለ መልኩ ወደ ተጋጣሚ ጎል ክልል ለመቅረብ ጥረት ያደረጉት ሰበታዎች በ40ኛው ደቂቃ ፍፁም ገብረማርያም ባደረገው ሙከራ ጥሩ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ያሬድ ሀሰን ጥሩ አንድ ሁለት ተጫውቶ ወደፊት በመሄድ ያሻገረለትን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም አስቆጥሮ ሰበታን መሪ በማድረግ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሰበታዎች ዳንኤል ኃይሉን አስወጥተው ዳዊት እስጢፋኖስን በማስገባት ይበልጥ ጨዋታውን ለመቆጣጠር አስበው ቢገቡም ባህር ዳሮች በፍጥነት ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን ሌላ መልክ ሰጥተውታል። በ 50ኛው ደቂቃ ፍፁም ዓለሙ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ወደ ውስጥ ያሻገረው ኳስ በያሬድ ሀሰን ተጨርፎ አቅጣጫውን በመሳት ወደ ጎልነት ተቀይሯል።

ከጎሉ 10 ደቂቃዎች በኋላ ሰበታ ከተማዎች በድጋሚ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል በረዳት ዳኛ ከጨዋታ ውጪ ውሳኔ ተሽሮባቸዋል። ቡልቻ ሹራ በአስደናቂ ሁኔታ ከግራ መስመር አጥብቦ በመግባት ወደ ጎል የላከውን ኳስ የጎሉ መስመርን ከማለፉ በፊት ፍፁም ገብረማርያም ወደ ጎልነት ቢለውጥም ጨዋታ ውስጥ የነበረው ፍፁም ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል የተሻረው ኳስ የጨዋታው ዐቢይ ክስተት ነበር።

በ68ኛው ደቂቃ ባህር ዳሮች ወደ መሪነት የተሸጋገሩበትን ጎል አስቆጥረዋል። ፍፁም ከግራ መስመር በጥሩ ሁኔታ በመግፋት ያሻገረውን ኳስ ከተከላካዮች ትኩረት ነፃ የነበረው ሳለአምላክ ተገኝ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ከአራት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ለፍፁም ጎል አመቻችቶ ኋላ ላይ ራሱ ላይ ጎል ያስቆጠረው ያሬድ ሀሰን ከረዳት ዳኛው ጋር በፈጠረው ምልልስ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ከቀይ ካርዱ በኋላ ባህር ዳሮች ይበልጥ በነፃነት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን በ76ኛው ደቂቃ አብዱልባሲጥ ከማል ከተከላካዮች ተቀብሎ ወደፊት ለማምራት ያደረገው ጥረት በአህመድ ረሺድ ተቋርጦ ኳሱ ምንይሉ ጋር ሲደርስ አጥቂው በቀጥታ መትቶ የጎል ልዩነቱን አስፍቷል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተገባዶ በተጨማሪ ደቂቃ ደግሞ መሳይ ጳውሎስ በምንይሉ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ግርማ ዲሳሳ ወደ ጎልነት ለውጦት ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ