ሪፖርት| ፋሲል የሆሳዕናን ያለመሸነፍ ጉዞ በመግታት የሊጉን መሪነት ተረክቧል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ጎል ሆሳዕናን አሸንፏል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከወልቂጤው ጨዋታ ሦስት ለውጦች በማድረግ ሳሊፉ ፎፋና፣ ቢስማርክ አፒያ እና ዱላ ሙላቱ ወጥተው ቴዎድሮስ በቀለ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ካሉሻ አልሀሰንን የማካተት ጨዋታውን ሲጀምር በፋሲል ከነማ በኩል ሲዳማ ቡናን ማሸነፍ ከቻለበት ጨዋታ ጉዳት በገጠመው ሰዒድ ሀሰን ምትክ እንየው ካሣሁን ብቻ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

ፋሲል ከነማዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በፈጠሯቸው መልካም የጎል ዕድሎች በጀመረው ጨዋታ ዐጼዎቹ ቀዳሚ ሊሆኑባቸው የሚችሉባቸው ጥቂት የማይባሉ አጋጣሚዎች አግኝተዋል። በተለይም ሙጂብ ቃሲም በተከታታይ ሦስት ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች የደረሱት ቢሆንም በአግባቡ አልተጠቀመባቸውም። በተጨማሪም እንየው ካሣሁን ከሱራፌል የተቀበለውን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል የወጣበት ሙከራ እንዲሁም ሱራፌል ዳኛቸው ከማዕዘን ምት ከአምሳሉ ጋር ተቀባብሎ የሞከረውና ደረጄ ዓለሙ የመለሰበት ሙከራዎች ለዚህ እኖደ ማሳያ የሚቀርቡ ነበሩ።

በፋሲል የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና በሆሳዕና ክፍተት የመዝጋት እንቅስቃሴ የቀጠለው ጨዋታ ከመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች በኋላ እምብዛም የሚጠቀስ የማጥቃት አጋጣሚዎች ያልታዩበት ሲሆን ይህቁንም መጎሻሸሞች የበዙበት ሆኖ አልፏል። በዚህም ተጨማሪ ሙከራዎች ሳንመለከት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ ተመሳሳይ ይዘት በነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ለረጅም ደቂቃዎች የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ያልታየበት ሲሆን ፋሲሎች ከሱራፌል መነሻቸውን ካደረጉ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ ዋነኛ አጥቂዎቻቸውን በህመም ምክንያት ያላሰለፉት ሆሳዕናዎች በረጅም ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ያደረጉት ሙከራ ስኬታማ አልነበረም።

የሆሳዕና የጥንቃቄ አጨዋወት እና የተከላካዮች ወጥመድ በመስበር ተደጋጋሚ ዕድሎችን ሲያገኝ የነበረው ሙጂብ ቃሲም በ69ኛው ደቂቃ ከሱራፌል የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ መትቶ ተስፋዬ ደርቦበት ሲወጣበት በ80ኛው ደቂቃ የጨዋታውን ልዩነት ፈጣሪ ጎል አስቆጥሯል። ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ፊት ያሻገረውን ኳስ ሙጂብ አምልጦ በመውጣት በደረጄ ዓለሙ መረብ ላይ አሳርፎ የዓመቱን ዘጠነኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ሙጂብ ጎሉ ከተቆጠረበት መንገድ ጋር የሚመሳሰል አጋጣሚ አግኝቶ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል የወጣበት ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ እጅጉን ተዳክመው የታዩት ሆሳዕናዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም አማኑኤል ጎበና ከግማሽ ጨረቃ አካባቢ መትቶ በተከላካዮች ተጨርፎ ከወጣበት ኳስ ውጪ የጠራ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው በፋሲል 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ዐፄዎቹ ሊጉን የሚመሩበት፤ ነብሮቹ የዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ያስተናገዱበት ሆኖም ተመዝግቧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ